:::ዜናዎች:::

:::ያግኙን :::

ርዕሰ አንቀጽ

ወጣቱ ወዴት ነው መሄድ ያለበት)
የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በሃይማኖት ፍቅር በነደዱ፣ ለተጋድሎ ራሳቸውን በሰጡ የአባቶቻቸውን ታሪክ ለመድገም በቆረጡ ታሪክ ሠሪ ወጣቶች የተሞላ ነው፡፡ እነ አቤልን፣ እነ ይስሐቅን፣ እነ ያዕቆብን፣ ነቢዩ ዳንኤልን እና ሠለስቱ ደቂቅን፣ ባሮክን እና አቤሜሌክን በብሉይ ኪዳን እናገኛቸዋለን፡፡
ተጨማሪ

 
  
  ራእይ
 
የጥያቄዎ መልስ
  ሊቀ ጳጳሱን ይጠይቁ
 
 
 
ዜናዎች
 
 
ሀገረ ስብከቱን ለመደገፍ የተጠራ ዝግጅት ተካሄደ

ዋሽንግተን ዲሲ (ነሐሴ 17/2000 ዓ.ም)፡- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የዲሲና አካባቢውን ሀ/ስብከት አቅም ለማጎልበት የተጠራ ዝግጅት በውጤት ተጠናቀቀ፡፡ቅዳሜ ነሐሴ 17/ 2000 ዓ.ም በዋሽንግተን ዲሲ በተዘጋጀው በዚህ ዝግጅት የሀገረ ስብከቱ 

ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃምና የሰሜን ምዕራብ ሸዋ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ ተገኝተው ትምህርት፣ ምክርና ቡራኬ ሰጥተዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ አብርሃም በትምህርታቸው ስለ መልካም ነገር ለምን ትጠይቀኛለህ (ማቴ 19፡17) የሚለውን አምላካዊ ቃል በመጥቀስ ሰፊ ትምህርት የሰጡ ሲሆን የእመቤታችንን በዓል ለማክበር ከሄዱበት ሐዋርያዊ አገልግሎት ሲመለሱ ዕረፍት ላግኝ ሳይሉ ወደ ጉባዔው የመጡት ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስም በበኩላቸው የተጀመረው ታላቅ ሥራ እንዲቀጥልና ከግብ እንዲደርስ ሁሉም እንዲራዳ በሰጡት አባታዊ ምክር አሳስበዋል፡፡
በጉባዔው ላይ የተገኙ ምእመናን የእጅ እና የአንገት ወርቃቸውን ሳይቀር በመለገስ ሀገረ ስብከቱ ሥራውን እንዲጀምርና ታላቋ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በውጪው ዓለም የምትፈጽመው ሐዋርያዊ አገልግሎት እንዲሳካ ያላቸውን መልካም ምኞት ገልጸዋል፡፡ በዝግጅቱ ላይ አስተያየታቸውን እንዲሰጡ የተጠየቁ ምእመናን ሀገረ ስብከቱ እንዲህ ያለውን ተመሳሳይ ዝግጅት ማካሄዱን እንዲቀጥልበት አሳስበዋል፡፡

 

ሀገረ ስብከቱ ያዘጋጀው ጉባኤ ተካሄደ

የዋሽንግተን ዲሲ እና አካባቢዋ ሀገረ ስብከት ያዘጋጀው መንፈሳዊ ጉባኤ ነሐሴ አራት ቀን ተካሄደ፡፡ መምህራን እና መዘምራን በተሳተፉበት በዚህ ጉባኤ ኬአድባራቱ የመጡ አያሌ ምእመናን ተሳትፈውታል፡፡  

ስለ ሀገረ ስብከቱ አጠቃላይ እንቅስቃሴ፣ስለ ሀገረ ስብከት አስፈላጊነት፣የቤተ ክርስቲያንን አንድነት ለማጠናከር መደረግ ስላለበት ነገር ገለጻ የተደረገ ሲሆን ምእመናኑም በተጀመረው በጎ አገልግሎት ገብተው ለመሳተፍ ዝግጁ መሆቸውን ገልጠዋል፡፡

የተጀመረውን በጎ አገልግሎት በሚገባ ባለመረዳት እየተሳሳቱ ያሉትን ወገኖች በማስረዳት እና ከስሕተት በመጠበቅ ረገድ ምእመናኑ የበኩላቸውን እንደሚያደረጉ የገለጡ ሲሆን ለወደፊቱ የቤተ ክርስቲያኒቱን አንድነት ይበልጥ ለማጠናከር ተመሳሳይ ጉባኤያት በየጊዜው መደረግ እንዳለባቸው ሃሳብ ሰጥዋል፡፡ 

 

የዋሽንግተን ዲሲ እና አካባቢው ሀገረ ስብከትን ለማጠናከር ጥረት እየተደረገ ነው

ቤተ ክርስቲያን በምድረ አሜሪካ አገልግሎት የጀመረችበት ሃምሳኛ ዓመት በሚከበረበት ዓመት ዋዜማ የዲሲ እና አካባቢው ሀገረ ስብከትን በአደረጃጀት፣ በቁሳቁስ እና በሰው ኃይል ለማጠናከር እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ አስታወቁ፡፡ 

ብጹዕ አቡነ አብርሃም የሰሜን ምሥራቅ፣የደቡብ ምሥራቅ እና የመካከለኛው አሜሪካ የኒውዮርክ ሀገረ ስብከት እና የዋሽንግተን ዲሲ እና አካባቢው ስብከት ሊቀ ጳጳስ እንደገለጡት እስካሁን ድረስ ሀገረ ስብከቱ የራሱ የሆነ ጽ/ቤት፣ የተሟላ የሰው ኃይል እና በቂ የሆነ ድርጅት የለውም፡፡ በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ የነበረው ፈተና ቀደምት አበው ይህንን ለመሥራት እንዳይችሉ አድርጓቸው ቆይቷል፡፡ አሁን ግን ካህናትን እና ምእመናንን በማስተባበር ሀገረ ስብከቱን የማዋቀር እና የማደራጀት ሥራ በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡ 

እስከ አሁን ድረስ ሀገረ ስብከቱን በአሜሪካ መንግሥት በሕጋዊ መንገድ የማስመዝገብ፣ መዋቅሩን በቃለ ዐዋዲውን መሠረት የማዘጋጀት፣ ጊዜያዊ መሥራች ኮሚቴውን የማቋቋም፣ ለኮሚቴው የሰው ኃይል የመደልደል እና ዝርዝር ሥራውን የማውጣት ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ 

ሀገረ ስብከቱን የማደራጀቱ ሥራ ያስፈለገው፣ሃይማኖቱን እና ቀኖናውን ለመጠበቅ እና ለማስጠበቅ፣ በአብያተ ክርስቲያናት መካከል የሚኖረውን አንድነት ለማሳካት፣ በአካባቢው ያለውን የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴ ለማቃናት፣ በእናት ቤተ ክርስቲያንና አሜሪካ በሚኖረው ምእመን መካከል ያለውን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር፣ ኤግዚቢሽኖችን፣ ዐውደ ጥናቶችን እና ሴሚናሮችን በማዘጋጀት ወጣቱ ትውልድ ስለ ቤተ ክርስቲያኑ የሚረዳበትን መንገድ ለማመቻቸት፣ በአብያተ ክርስቲያናት መካከል አንድ ወጥ እና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን የጠበቀ አገልግሎት ለመስጠት መሆኑን ብጹዕ አቡነ አብርሃም ገልጠዋል፡፡

በዚህ ባለንበት በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ ካህናት እና ምእመናን ሕዝቡ ስለ ቤተ ክርስቲያኑ እንዲያውቅ፣ ከአጽራረ  ቤተ ክርስቲያን እንዲጠበቅ፣ የጥምቀት፣ የፍትሐትና የተክሊል አገልግሎት እንዲያገኝ ሲያደርጉ በመኖራቸው፣ ከዚህም በላይ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እንዲስፋፋና አብያተ ክርስቲያናት እንዲመሠረቱ ታላቅ ሚና በመጫወታቸው ሊመሰገኑ ይገባል፡፡ እኛም ይህንን አገልግሎት በተቀናጀ መልኩ እንዲፈጸም በማድረግ ልናግዛቸው ነው ሀገረ ስብከቱን ማቋቋም ያስፈለገን፡፡  

ሀገረ ስብከቱን የተሟላ ለማድረግ ሦስት መሟላት ያለባቸው ነገሮች እንዳሉ ብጹዕ አባታችን ገልጠዋል፡፡ እነዚህም ጽ/ቤት፣ መንበረ ጵጵስና እና የመንበረ ጵጵስና ቤተ ክርስቲያን ናቸው፡፡ ጽ/ቤቱ የሀገረ ስብከቱን እንቅስቃሴ የሚመራው ተቋማዊ ሥራ የሚሠራበት ሲሆን መንበረ ጵጵስናው ደግሞ የሊቀ ጳጳሱ ማረፊያ እና እንግዶችን የማስተናገጃ ቦታ ነው፡፡ ሊቀ ጳጳሱ ታቦት የሚባርኩበት፣ክህነት የሚሰጡበት፣ቀድሰው የሚያቆርቡበት እና የሚጸልዩበት ደግሞ የመንበረ ጵጵስና ቤተ ክርስቲያን በሥሩ ይኖረዋል፡፡ 

ሀገረ ስብከቱም ሆነ የመንበረ ጵጵስናው ቤተ ክርስቲያን በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ባለቤትነት እና ንብረትነት የተመዘገበ ሲሆን ይህም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሀብት እና ንብረት ሆኖ በቤተ ክርስቲያኒቱ ቀኖና ብቻ የሚመራነው፡፡ 

በቅድስት ሀገር በኢየሩሳሌም የሚገኙ ሕንፃዎች እና ቤቶች እስከ ዛሬ ተጠብቀው አገልግሎት የሚሰጡት ባለቤትነታቸው የቤተ ክርስቲያኒቱ በመሆናቸው ነው፡፡ በግለሰቦች ቢያዙ ኖሮ አንድም ተሸጠው ያለበለዚያም ተወርሰው በተወሰዱ ነበር፡፡ ተከራካሪዎች እየተነሡ እንወስዳለን ባሉ ጊዜ እየተሟገተች ከዚህ ዘመን የደረሰችው ቤተ ክርስቲያኒቱ ናት፡፡ እኛም ልንሠራው የምንፈልገው እነዚያ ቀደምት አበው የሠሩትን ሥራ ነው፡፡ 

በዚህ አገልግሎት የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች የሆኑ ሁሉ ገብተው እንዲሳተፉ እና እናት ቤተ ክርስቲያናቸው ደረጃውን የጠበቀ፣ከአኃት ቤተ ክርስቲያን ጋር ክብሩን ጠብቆ ሊገናኝ የሚችል፣የቤተ ክርስቲያኒቱን አጠቃላይ አገልግሎት የሚያስተባብር ሀገረ ስብከት እንዲኖራት አስተዋጽዖ እንዲያደርጉ ብጹዕ አቡነ አብርሃም ጥሪ አድርገዋል፡፡ 

በአንድ ሀገረ ስብከት የቅዱስ ሲኖዶስ ወኪል ሊቀ ጳጳሱ ነው፡፡ ሊቀ ጳጳሱ አገልግሎታቸውን የተሳካ ለማድረግ እና ቤተ ክርስቲያንን ወደ ላቀ ዕድገት ለማሸጋገር ደግሞ የካህናት እና የምእመናን ድጋፍ ያስፈልጋል፡፡ ይህንን ድጋፍ ለማቀናጀት እና አገልግሎቱን ቀልጣፋ እና አንድ ወጥ ለማድረግም የተደራጀ ቢሮ እና የአሠራር ሥርዓት ያስፈልገናል፡፡ ለዚህ ነው ሀገረ ስብከቱን ማደራጀት የፈለግነው፡፡ 

ይሄው በዋሽንግተን የተጀመረው የማጠናከር ሥራ ሌሎች በአሜሪካ የሚገኙ አህጉረ ስብከትን ለማጠናከር ተባብሮ በመሥራት እንደሚቀጥል ብጹዕነታቸው አያይዘው ገልጠዋል፡፡

  Listen Lesson of the week
  Listen Mesbak of the week
  Downlad Songs and Publications
  Discover Ethiopian Orthodox Church History
  Preaching of the week
 
  www.eotc-mkidusan.org
 
www.mahiberekidusan.org
  www.radiotewahedo.org
  www.tewahedomedia.org
Home| Feedback| Webmaster
EOTC-DC Diocese., All Rights Reserved