:::ዜናዎች:::

:::ያግኙን :::

ርዕሰ አንቀጽ

ወጣቱ ወዴት ነው መሄድ ያለበት)
የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በሃይማኖት ፍቅር በነደዱ፣ ለተጋድሎ ራሳቸውን በሰጡ የአባቶቻቸውን ታሪክ ለመድገም በቆረጡ ታሪክ ሠሪ ወጣቶች የተሞላ ነው፡፡ እነ አቤልን፣ እነ ይስሐቅን፣ እነ ያዕቆብን፣ ነቢዩ ዳንኤልን እና ሠለስቱ ደቂቅን፣ ባሮክን እና አቤሜሌክን በብሉይ ኪዳን እናገኛቸዋለን፡፡Ý
ተጨማሪ

 
 
  ራእይ
 
የጥያቄዎ መልስ
  ሊቀ ጳጳሱን ይጠይቁ
 
 
ገረ ስብከታችን

ሀገረ ስብከት ታሪኩ፣ተግባሩ እና አስፈላጊነቱ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቃለ ዐዋዲ ምዕራፍ ስድስት፣ ዐንቀጽ ሠላሳ ስምንት እስከ አርባ አምስት ድረስ በተዘረዘረው መሠረት ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጠቅላይ ጽ/ቤት ቀጥሎ በቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅር መሠረት የመንበረ ጵጵስና ሀገረ ስብከት መሥርቶ እና አጠናክሮ መሥራቱ ለቤተ ክርስቲያን አንድነት አስፈላጊ እና ወሳኝ ነው፡፡ 

በቃለ ዐዋዲው ዐንቀጽ አርባ ሦስት ቁጥር አንድ ላይ እንደ ተገለጠው «የመንበረ ጵጵስና ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት በሀገረ ስብከቱ ክልል ውስጥ ለሚገኙ ገዳማት፣ አድባራት እና የገጠር አብያተ ክርስቲያናት እንዲሁም በየደረጃው ለተቋቋሙት ሰበካ መንፈሳውያን ጉባኤያትና ለወረዳ ቤተ ክህነት የሥራ አመራርና ከፍተኛ የአስተዳደር ኃላፊነት ያለው መሥሪያ ቤት ነው» 

በእንግሊዝኛው «ዳዮሰስ» የሚለው ቃል dioikesis ከሚለው የግሪክ ቃል የመጣ ነው፡፡  አሥራ ስድስተኛው የኒቂያ ጉባኤ ቀኖና ይህንን ቃል«በአንድ ሊቀ ጳጳስ የሚመራ ክልል» በሚል እንደገለጠው ሀገረ ስብከት ማለት በአንድ ሊቀ ጳጳስ የሚመራ አንድ አካባቢ ማለት ነው፡፡ 

  ‘The Dictionary Of Church Terms’ የሚለው የግብጽ ቤተ ክርስቲያን መዝገበ ቃላት ደግሞ «The area of limits of jurisdiction of a diocesan bishop. It is usually divided into parishes.» መሆኑን ያስገነዝባል፡፡

ሀገረ ስብከት ለመጀመርያ ጊዜ በሥራ ላይ የዋለው ቅዱሳን ሐዋርያት የጌታችንን ትምህርት ተግባራዊ ለማድረግ ዓለምን ዕጣ በዕጣ ተከፋፍለው ለማስተማር በወጡ ጊዜ ነው፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያት ይመቻል፣ አይመችም ሳይሉ በተሠማሩበት ሀገረ ስብከት ገብተው አብያተ ክርስቲያናትን በመትከል፣ ምእመናንን አስተምረው በማጥመቅ፣ ካህናትን እና ዲያቆናትን በመሾም የወንጌልን ቃል ለዓለም አዳርሰዋል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ በሮም ሀገረ ስብከቱ፣ ዮሐንስ ወንጌላዊው በታናሽ እስያ ሀገረ ስብከቱ፣ ቶማስ በሕንድ ሀገረ ስብከቱ፣ማርቆስም በእስክንድርያ የሠሩት ሥራ ለዚህ ማስረጃችን ነው፡፡ 

 በግብጽ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ መጀመርያ የነበረው የእስክንድርያ መንበር ብቻ ሲሆን በኋላ ግን እስክንድርያ የፓትርያርኩ መንበር ሆና በየአካባቢው አህጉረ ስብከት ተመሠረቱ፡፡ ለምሳሌ በ320 ዓ.ም በተካሄደው የእስክንድርያ ጉባኤ ከአንድ መቶ በላይ ጳጳሳት ተገኝተው ነበር፡፡ 

በኢትዮጵያውያን ነገሥታት እና ሕዝብ በጎ ፈቃድ እና አርቆ አስተዋይነት ወደ እስክንድርያ ተልኮ ለጵጵስና የበቃው የመጀመርያው ጳጳስ ፍሬምናጦስ ሀገረ ስብከት «ጳጳስ ዘአኩስም ወዘኩላ ኢትዮጵያ» የሚል ነበር፡፡ ከእርሱ በኋላ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ሥር እንደ አንድ ሀገረ ስብከት ሆና ከአንድ ሺ ዘመናት በላይ ቆይታለች፡፡  

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል በተለያዩ ጊዜያት ከአንድ በላይ ሊቃነ ጳጳሳት ተሾመው መጥተው ስለነበር ከአንድ በላይ አህጉረ ስብከት እንደነበራት ይጠቁማል፡፡ በዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመነ መንግሥት በ1438 ዓም ሁለት ሊቃነ ጳጳሳት ከግብጹ ፓትርያርክ ዮሐንስ 14ኛ ተሾመው መጥተው ነበር፡፡ እነዚህ ሊቃነ ጳጳሳት አባ ሚካኤል ለአምሐራ፣ አቡነ ገብርኤልም ለሸዋ ሀገረ ስብከት ጳጳስ ሆነው ተመደቡ፡፡ ይህም በወቅቱ የነበረውን የሀገረ ስብከት አደረጃጀት ያመለከታል፡፡  

በዐፄ ዮሐንስ ጊዜም በ1874 ዓ.ም አራት ጳጳሳት ከግብጽ መጥተው አቡነ ጴጥሮስ የኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ፣ አቡነ ማቴዎስ የሸዋ ጳጳስ፣ አቡነ ሉቃስ የጎጃም፣ አቡነ ማርቆስ የበጌምድር ሀገረ ስብከት ጳጳስ ሆነው ተሾመዋል፡፡ እነዚህ አበው በውል የተለየ ቦታ ተከልሎ ተሰጥቷቸው እንደነበር ጸሐፌ ትእዛዝ ገብረ ሥላሴ በጻፉት «ታሪከ ዘመን ዘዳግማዊ ምኒልክ» በተባለው መጽሐፋቸው የአቡነ ማቴዎስን ሀገረ ስብከት ሲዘረዝሩ «ሸዋን ከበሽሎ ወዲህ መደብ አድርገው የጁን፣ ዋድላን፣ ደላንታን፣ ዳውንትን፣ ግራ መቄትን፣ ከበጌምድር መጃን፣ ስዲን፣ ፎገራን፣ ጭህራን፣ደምቢያን፣ አርማጭሆን፣ መረባን፣ ጃን ፈቀራን፣ ጃንዋራን፣ ቆላ ወገራን፣ ጠገዴን፣ ወልቃይትን» እያለ ይዘረዝራል፡፡ 

በግርማዊ ቀዳማዊ ንጉሠ ነገሥት ዐፄ  ኃይለ ሥላሴ ዘመን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የመጀመርያዎቹን ጳጳሳት ስታገኝ የታወጀው ዐዋጅ ዐንቀጽ አንድ «የኢትዮጵያ የመላው ሊቀ ጳጳሳት በአቡነ ቄርሎስ ሆኖ ከውስጡ ክፍል ስብከትም ኢትዮጵያ መሐል ሆኖ ደቡቡ ለአቡነ ሳዊሮስ፣ ምዕራቡ ለአቡነ አብርሃም፣ ምሥራቁ ለአቡነ ጴጥሮስ፣ አዜቡ ለአቡነ ሚካኤል፣ ሰሜኑ ለአቡነ ይስሐቅ ይሁን» ይላል፡፡ ይኼው ዐዋጅ የየአንዳንዱን ጳጳስ የሀገረ ስብከት ክልል ዝርዝር እና የመንበረ ጵጵስናውን ማረፊያ ከተማ ይተነትናል፡፡ 

በጣልያን ዘመን ግብፃዊው አቡነ ቄርሎስ ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት እና ጳጳሳት ተሰባስበው ብጹዕ አቡነ አብርሃምን ሊቀ ጳጳስ አድርገው አምስት ጳጳሳትን ሲሾሙ አዳዲስ አህጉረ ስብከት ተመሠረቱ፡፡ አቡነ ዮሐንስ የሸዋ፣ አቡነ ማርቆስ የኤርትራ፣ አቡነ ማቴዎስ የወሎ፣ አቡነ ገብርኤል የጎንደር እንዲሁም አቡነ ሉቃስ የወለጋ አህጉረ ስብከት ጳጳሳት ሆነው ተሾመዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የራስዋን አህጉረ ስብከት መመሥረት የጀመረችው ከራስዋ ልጆች መካከል ፓትርያርክ ባገኘች ጊዜ ነበር፡፡ በ1943 ዓም የመጀመርያው ኢትዮጵያዊ ፓትርያርክ ሆነው የተሾሙት ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ አቡነ ታዴዎስን ለጎሬ፣ አቡነ ገብርኤልን ለወሎ፣ አቡነ ማርቆስን ለኤርትራ፣ አቡነ ፊልጶስን ለኢየሩሳሌም፣ አቡነ ጎርጎርዮስን ለከፋ ጳጳሳት አድርገው ሾመው ነበር፡፡ ይህም አዳዲስ አህጉረ ስብከት መመሥረታቸውን ያመለክታል፡፡ በ1948 ዓ.ም ትግራይ በሀገረ ስብከትነት ተቋቁሞ ብጹዕ አቡነ ዮሐንስ ተሾመውበታል፡፡ 

በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የአህጉረ ስብከት ቁጥር በየጊዜው እያደገ መጥቶ፣ ብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ «የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ» በተሰኘው መጽሐፋቸው እንደገለጡት፣ በ1974 ዓ.ም የአህጉረ ስብከቱ ዕድገት ወደ አሥራ ዘጠኋ ያህል ደርሶ ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜ ደግሞ «የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከልደተ ክርስቶስ እስከ 2000 ዓ.ም» የተሰኘው  የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት መጽሐፍ እንደሚገልጠው አርባ በሀገር ውስጥ፣ ስምንት ከሀገር ውጭ፤ በድምሩ አርባ ስምንት አህጉረ ስብከት ይገኛሉ፡፡ 

አህጉረ ስብከት በዳያስጶራ

/ዳያስጰራ፡— ከሀገሩ ወጥቶ በዝርወት የሚኖር ሕዝብ/

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከሀገር ውጭ የመጀመርያውን ሀገረ ስብከት ያቋቋማቸው ነሐሴ 28 ቀን 1943 ዓ.ም ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ አቡነ ፊልጶስን የኢየሩሳሌም ሊቀ ጳጳስ አድርገው በሾሟቸው ጊዜ ነው፡፡ በምዕራቡ ዓለም የነበረው የቤተ ክርስቲያን እንቅስቃሴ በ1945 ዓ.ም ሲጀመር የምዕራቡ ዓለም «ምዕራባዊው ንፍቀ ክበብ፣ Western Hemisphere» በሚል አንድ ሀገረ ስብከት ነበር፡፡ በኋላ ግን እኤአ በ1992 ዓ.ም ቅዱስ ሲኖዶስ ባደረገው ጉባኤ ይህንን ሀገረ ስብከት አራት አህጉረ ስብከት እንዲሆን ተደረገ፡፡ ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ እና ካናዳ፣ የካሪቢያን ደሴቶች እና ደቡብ አሜሪካ፣ ምዕራብ አውሮፓ እና ምሥራቅ አፍሪካ ሆነው ሊቃነ ጳጳሳት ተሾሙባቸው፡፡ 

እኤአ በ1995 የዩናየትድ ስቴትስ እና የካናዳ ሀገረ ስብከት ወደ ሁለት ተከፈሉ፡፡ ካናዳ ለብቻው ዩናይትድ ስቴትስም ለብቻው ሆኖ ተቋቋመ፡፡ በ1998 ዓ.ም ደግሞ ዩናይትድ ስቴትስ ወደ ሦስት ተከፋፍሎ የካሊፎርኒያ እና አካባቢው፣ ዋሽንግተን ዲሲ እና አካባቢ እንዲሁም የሰሜን ምሥራቅ፣ የደቡብ ምሥራቅ እና የመካከለኛው አሜሪካ የኒውዮርክ ሀገረ ስብከት ተብሎ ሦስት ሊቃነ ጳጳሳት ተሾሙበት፡፡ 

በ1985 ዓም የአፍሪካ፣ በ1997 ዓም የዓረብ ኤምሬትስ እና የአካባቢው ሀገረ ስብከት፣ በ1998 ዓም የአውስትራልያ ሀገረ ስብከት፣ በ1998 ዓም የደቡብ አፍሪካ አሀጉረ ስብከት ከኢትዮጵያ ውጭ ተቋቁመዋል፡፡ 

ይህም ቤተ ክርስቲያናችን ከሀገር ውጭ እየሠራችው ያለው ሃይማኖታዊ እና ማኅበራዊ አገልግሎት እያደገ እና እየተስፋፋ መምጣቱን ያመለክታል፡፡

የሀገረ ስብከት ተግባር

ሀገረ ስብከት በአንድ የተወሰነ ክልል ቤተ ክህነቱን ወክሎ የሚሠራ ተቋም ሲሆን፣ ሃይማኖቱን እና ቀኖናውን ለመጠበቅ እና ለማስጠበቅ፣ ከክርስቶስ ጀምሮ የመጣውን ሀብተ ክህነት ለመጠበቅ እና ለማስተላለፍ፣ ስብከተ ወንጌል እንዲስፋፋ፣ ገዳማት እና አድባራት እንዲረዱ፣ አብያተ ክርስቲያናት እንዲተከሉ፣ ምእመናን ተገቢውን አገልግሎት እንዲያገኙ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሕጋዊ መብት እንዲከበር፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልግሎት ወጥ እና ሥርዓቱን የጠበቀ እንዲሆን፣ የካህናት አስተዳደር እና አገልግሎት በቤተ ክርስቲያኒቱ ሕግ መሠረት እንዲሆን፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሀብት እና ንብረት በሕግ እና በሥርዓት መሠረት እንዲጠበቅ፣ ምእመናን በቤተ ክርስቲያኒቱ ተገቢውን አገልግሎት እንዲያገኙ እና እንዲሰጡ ማድረግ ዋና ዋናዎቹ ተግባሮቹ ናቸው፡፡ 

አንድ ሀገረ ስብከት በውስጡ የሀገረ ስብከት ጽ/ቤት እና መንበረ ጵጵስናን ይይዛል፡፡ የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት የሀገረ ስብከቱን ተቋማዊ ሥራ የሚሠራ ሲሆን መንበረ ጵጵስናው ደግሞ የሊቀ ጳጳሱ ማረፊያ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ መንበረ ጵጵስናው ከቤተ ክርስቲያን አጠገብ እንዲሆንና ያም ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳሱ ለሚያደርጉት መንፈሳዊ አገልግሎት /ታቦት መባረክ፣ ክህነት መስጠት፣ ቅዳሴ፣ ወዘተ/ አገልግሎት እንዲሰጥ ይደረጋል፡፡  

አንድ ሀገረ ስብከት ያለ መንበረ ጵጵስና ቤተ ክርስቲያን መመሥረት እንደማይቻል በሀገራችንም ከመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ጀምረን በየአህጉረ ስብከቱ ልንጠቅሳቸው የምንችል ምሳሌዎች አሉ፡፡ በቀድሞ ጊዜ የሰላ ደንጋይ ማርቆስ እና የመናገሻ ማርቆስ አብያተ ክርስቲያናት የግብጻዊው ሊቀ ጳጳስ የአቡነ ማቴዎስ መንበረ ጵጵስናዎች ነበሩ፡፡በአዋሳ ሀገረ ስብከት የቅዱስ ገብርኤልን፣ በምዕራብ ጎጃም ሀገረ ስብከት የፈለገ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያንን፣ በምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት የደብረ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያንን፣ በባሌ ጎባ ሀገረ ስብከት የመድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያንን መጥቀስ ይቻላል፡፡

የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት በሥሩ ልዩ ልዩ መምሪያዎችን የሚይዝ ሲሆን የአካባቢውን ቤተ ክርስቲያናዊ አገልግሎት በተቀናጀ መልኩ ይመራል፡፡    

ከሀገረ ስብከቱ ቀጥሎ የወረዳ ቤተ ክህነቶች በሊቃነ ካህናት መሪነት ይቋቋማሉ፡፡ እነዚህም በአንድ የቅርብ አካባቢ ያለውን አገልግሎት የሚያስተባብሩ ናቸው፡፡ እስካሁን ድረስ በአሜሪካ ከሀገረ ስብከት በታች የሚገኙ ወረዳ ቤተ ክህነቶች አልተቋቋሙም፡፡ ለወደፊት ግን እንደ አስፈላጊነቱ እና እንደ ይዘቱ በቃለ ዐዋዲው መሠረት የሚቋቋሙ ይሆናሉ፡፡ ይህም የቤተ ክርስቲያኒቱን ሃይማኖታዊ እና አስተዳደራዊ አንድነት ለመጠበቅ ይበልጥ አጋዥ ኃይል ይሆናል፡፡ 

 በአሜሪካ የሀገረ ስብከት መጠናከር ለምን ያስፈልጋል

 1. በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን አህጉረ ስብከት ማጠናከር የሚያስፈልግባቸው አያሌ ምክንያቶች አሉ፡፡ ለግንዛቤ ያህል ግን አሥራ አንዱን ብቻ እንመለከታለን፡፡ ሃይማኖቱ ባለበት የሀገረ ስብከቱ መኖር ሃይማኖታዊ ግዴታ ስለሆነ ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን የምትጓዘው ሐዋርያት በተጓዙበት መንገድ ነው፤ ሥርዓቷም ትወፊቷም፣ አሠራርዋም ሐዋርያዊ ነው፡፡ አባቶቻችን ሐዋርያት ወንጌል ሰብከው ሃይማኖት ያስፋፉት አህጉረ ስብከትን እየመሠረቱ በመሆኑ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ባለበት ሁሉ ሀገረ ስብከትን መመሥረት እና ማጠናከር ሃይማኖታዊ ግዴታ ነው፡፡
 2.   የቤተ ክርስቲያንን ዶግማ፣ ቀኖና እና ትውፊት በወጥነት ለማስጠበቅ፡  የአንዲት ቤተ ክርስቲያን ዶግማ፣ ሥርዓት እና ትውፊት ወጥ በሆነ መልኩ ሊጠበቅ የሚችለው አንድ ወጥ የሆነ የማስጠበቂያ መንገድ ሲኖራት ነው፡፡ ምእመናንን፣ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናትን እና ልዩ ልዩ ተቋማትን በአንድነት የሚያስተባብር አካል ከሌለ እነዚህ አካላት ሳይገናኙ፣ ሳይነጋገሩ፣ ሳይተጋገዙ እና ሳይግባቡ መጓዛቸው የማይቀር ነው፡፡ በዚህ መካከልም ሁሉም በየራሱ ስለሚጓዝ የቤተ ክርስቲያን ዶግማ ፣ቀኖና እና ትውፊት ለልዩነት እና ለብረዛ ይጋለጣል፡፡ ሰው ሁሉ ትክክል መሆኑ የታመነበትን ሳይሆን «በፊቱ መልካም መስሎ የታየውን ብቻ ያደርጋልና» መሳ. 21÷25፡፡
 3.  የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናትን አንድነት እና ትብብር ለማጠናከር፡— በአሜሪካ የሚገኙ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ብዙዎቹ ከሀገረ ስብከቱ ጋር ብዙም ግንኙነት ሳይኖራቸው በየራሳቸው የተመሠረቱ ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት በመካከላቸው የሚኖረውን ግንኙነት የሚያስተባበር፣ እንዲረዳዱ እንዲተባበሩ እና ለአንዲት ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በጋራ እንዲሠሩ የሚያደርግ ማዕከላዊ አካል የለም፡፡ የዚህ አለመኖር ደግሞ ተባብረን ልናመጣው እንችል የነበረውን ውጤት አስቀርቶብናል፡፡ ሌላው ቀርቶ እሑድ ወይንም ቅዳሜ የሚከበረውን የንግሥ በዓል አንኳን የሚያስተባብር እና የሚያቀናጅ ባለመሆኑ አንዱ ከሌላው ጋር እየተደራረበ ለተጋባዥ ጳጳሳት፣ ካህናት፣ መሪጌቶች እና መምህራን አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ ከሥርዓት እና ከሃይማኖትም አንጻር እገሌ ልክ ነው እገሌ ተሳስቷል የሚሉ እና በሀገረ ስብከት ከዚያም አልፎ በቅዱስ ሲኖዶስ ደረጃ ብቻ ሊፈቱ የሚችሉ ክርክሮች መፍትሔ አጥተው ሲያወዛግቡ እና ሲያከፋፍሉ ይኖራሉ፡፡ ማዕከላዊ አሠራርን የሚያስጠብቀው ሀገረ ስብከት መኖሩን ቢቀበሉ እና በዚያም ተገቢውን አገልግሎት ለማግኘት ፈቃደኛ ቢሆኑ ኖሮ ሳይርቅ በቅርቡ ሳይደርቅ በርጥቡ መፍትሔ በተሰጣቸው ነበር፡፡
 4.  ቀኖናውን ያልጠበቀ አሠራርን ለመከላከል፡—  አንድ ወጥ አሠራር በማይኖር ጊዜ ሁሉም እንደፈለገው በመሰለው መንገድ የመጓዝ ነገር ይጀመራል፡፡ እንደ ቤተ ክርስቲያናችን ቀኖና አንዲት ቤተ ክርስቲያን ያለ ሊቀ ጳጳሱ ፈቃድ እና ቡራኬ አትቋቋምም፡፡ ዛሬ ግን በቤተ ክርስቲያን ሕይወት ጥቂት ጊዜ እንኳን ያልቆዩ አንድ እና ሁለት ሰዎች እየተነሡ «ቤተ ክርስቲያን ከፈትን» የሚሉበት አሳዛኝ ነገር ከምናይበት ዘመን ደርሰናል፡፡ እንኳንስ ምእመናን ብቻቸውን ይቅር እና ቅዱስ ጳውሎስ እና በርናባስ እንኳን አሕዛብን አስተምረው እና አሳምነው ቤተ ክርስቲያን ሥሩልን ብለው በጠየቋቸው ጊዜ የመጀመርያይቱን ቤተ ክርስቲያን ሲመሠርቱ ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስን እና ሌሎችን ሐዋርያት ጠይቀው በፈቃደ እግዚአብሔር እና በልዩ ገቢረ ተአምራት የመጀመርያዋ ቤተ ክርስቲያን መመሥረቷን ታሪክ ያስተምረናል፡፡
 5. የምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ጉዳዮችን ለማየት፡— ዛሬ በማዕከላዊ አስተዳደር በማይመሩም ሆነ በእናት ቤተ ከርስቲያን ሥር ነን በለው ሥርዐቱን በሚገባ በማይጠብቁት ዘንድ የምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን እና የክህነት ጉዳዮች ሲነሡ የሚታዩት በምእመናን ጉባኤ ሆኗል፡፡ ይህ ግን ከቀኖናው ውጭ ነው፡፡ በዓለም ባለው አሠራር እንኳን የበላይን ጉዳይ የበታች አያየውም፤ ከርሱ የሚበልጠው ካልሆነ በቀር፡፡ በመሆኑም በአጥቢያዎች መካከል፣ በካህናት መካከል እና በካህናት እና በምእመናን መካከል የሚነሡ ጉዳዮችን ለማየት የተጠናከረ ሀገረ ስብከት ያስፈልገናል፡፡
 6. ለአባቶች የአገልግሎት መንገድ ለማመቻቸት፡—  ከቅዱስ ሲኖዶስ ተልከው ለአገልግሎት የሚመጡ ሊቃነ ጳጳሳት አገልግሎታቸው ምቹ ፣ ቀልጣፋ እና ደረጃውን የጠበቀ የሚሆነው የሚያርፉበት በኣት፣ የሚጸልዩበት ጸሎት ቤት፣ የሚሠሩበት ቢሮ የሚያገለግሏቸው አርድእት ሲኖሩ ነው፡፡ ይህንን አመቻችቶ ቤተ ክርስቲያን የጣለችባቸውን አገልግሎት እንዲወጡ ለማድረግ ደግሞ የመንበረ ጵጵስና ሀገረ ስብከት ያስፈልጋል፡፡
 7. ቤተ ክርስቲያን ለምታደርገው ኢኩሜኒካል ግንኙነት መንገድ ለመጥረግ፡- በአኃት አብያተ ክርስቲያናት መካከል ለሚደረገው ሃይማኖታዊ  ግንኙነት፣ ከሌሎች ጋር ለሚደረገው ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ትብብር አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ቅዱስ ሲኖዶስን ወክለው መሥራት አይችሉም፡፡ ምክንያቱም ግንኙነቱ በሊቀ ጳጳስ ደረጃ መደረግ አለበትና፡፡ ግብጻውያን እንዲያውም ለዚሁ ተግባር በሊቀ ጳጳስ የሚመራ ጽ/ቤት በአሜሪካ አላቸው፡፡ በአሜሪካ የሚገኙ አምስቱ አኃት አብያተ ክርስቲያናትም ሆኑ ቀኖናውያን የሆኑ የኦርቶዶክስ ሊቃነ ጳጳሳት በየዓመቱ ጉባኤ ያደርጋሉ፤ ሃይማኖታዊ እና ማኅበራዊ በሆኑ ጉዳዮችም ይነጋገራሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በልዩ ልዩ መንገድ ይረዳዳሉ፡፡  ይህንን ግንኙነት መልከ ለማስያዝ፣ ደረጃውን ለማስጠበቅና ውጤታማ ለማድረግ   የተጠናከረ እና ከሌሎች በእኩልነት የተደራጀ  ሀገረ ስብከት ያስፈልገናል፡፡
 8.  በሀገር ቤት የሚገኙ ገዳማት እና አድባራትን በተጠናከረ መንገድ ለመርዳት፡— በሀገር ቤት የሚገኙ እና በችግር ላይ ያሉትን ገዳማት እና አድባራት በተበታተነ መንገድ ሳይሆን አንድ ወጥ እና ውጤት ሊያመጣ በሚችል መንገድ ለመርዳት እንዲቻል በማዕከላዊነት የሚያስተባበር እና የሚከታተል አካል ያስፈልገናል፡፡ ይህ አካል ደግሞ በአሜሪካ ያለውን አስተዋጽዖ የሚያስተባብር፣  ሠንሠለቱን ጠብቆ ከመንበረ ፓትርያርኩ ጋር በመገናኘት ሥራው እንዲፈጸም የሚያደርግ መሆን አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ በቤተ ክርስቲያኒቱ ቀኖና መሠረት ጉዳዩ የሚመለከተው በሀገረ ስብከት ደረጃ ነው፡፡
 9. ልዩ ልዩ አገልግሎቶችን ለማስተባበር፡—  አንድነትን ለማምጣት እና ተባብሮ ለቤተ ክርስቲያን ለማገልገል በማሰብ የተደራጁ አያሌ ማኅበራት፣ ተቋማት እና በጎ ፈቃደኞች በአሜሪካ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ማኅበራት እና አንድነቶች ከአጥቢያዎች ዐቅም እና ወሰን በላይ በመሆናቸው ላቅ ያለ አስተባባሪ እና አጋዥ አካል ያስፈልጋቸዋል፡፡ የእነዚህ ማኅበራት እና አንድነቶች አገልግሎት የተቃና፣ የተሳካ እና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን የጠበቀ እንዲሆን ለማድረግ ደግሞ ከሀገረ ስብከቱ የተሻለ መዋቅር አይገኝም፡፡ ሀገረ ስብከቱ ተደራጅቶ የአገልግሎት መሥመሩን በሚገባ ካልዘረጋ በቀር የእነዚህ ማኅበራት እና አንድነቶች አገልግሎት ዝርው ይሆናል፡፡ ከዋናው ግንድ የተለየ ቅርንጫፍ ነውና፡፡
 10. በትውልድ ኢትዮጵያውያን ያልሆኑትን ወገኖች ወደ ቤተ ክርስቲያን ለማቅረብ፡—  ኢትዮጵያውያን ያልሆኑ ወገኖች ወደ ቤተ ክርስቲያን ቀርበው፤ ወንጌል ተምረው፣ አምነው እና ተጠምቀው የዚህች ቤተ ክርስቲያን ልጆች እንዲሆኑ ማድረግ አንዱ ኃላፊነታችን ነው፡፡ የእነዚህ ወገኖቻችን ሱታፌ ደግሞ በማመን እና በመጠመቅ ማብቃት የለበትም፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱን ነባር ትምህርት ተምረው አሠረ ክህነቱንም መከተል አለባቸው፡፡ ይህ እንዲሆን ደግሞ ከገዳማት አድባራት፣ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ት/ቤቶች እንዲሁም ከቅዱስ ሲኖዶስ የሚያገናኛቸው አካል ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ የሀገረ ስብከቱ መጠናከር ወሳኝ ነው፡፡
 11. ገዳማት እና ማሠልጠኛዎችን ለማቋቋም እና ለመምራት፡—  አዲሱ ትውልድ ከገዳማዊ ሕይወት እና ሥርዓት ጋር እንዲተዋወቅ፣ ምእመናን ሱባኤ እንዲይዙበት፣ ጠበል ለመጠመቅ፣ ጸሎት ለማድረግ እና ከዚህ ዓለም ጭንቀት ራስን ለመፈወስ የሚያስችሉ ገዳማትን በምንኖርበት አሜሪካ ለመመሥረት እና ለማስተዳደር፣ ከዚያውም ጋር አያይዞ ማሠልጠኛዎችን በማቋቋም ካህናትን፣ ዲያቆናትን እና መምህራነ ወንጌልን ለማፍራት የበላይ ሆኖ የሚከታተለውና ሥርዓቱን የሚያስጠብቀው ሀገረ ስብከት ቀድሞ መደራጀት ይገባዋል፡፡

እነዚህ ከላይ የተገለጡት ብቻ ናቸው ማለት አይደለም፡፡ ሌሎች ቢዘረዘሩ የማያበቁ ምክንያቶችም አሉ፡፡ ለጠቢብ ግን እነዚህ ይበቁታል፡፡ 

በመሆኑም ሁላችንም አንድ ደረጃ ከፍ በማለት፣ያለንን ዕውቀት እና ገንዘብ በመለገስ ሀገረ ስብከቱን ለማደራጀት በሚደገረው ጥረት ታሪካዊ ተሳታፊዎች ልንሆን ይገባናል፡፡ 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

  Listen Lesson of the week
  Listen Mesbak of the week
  Downlad Songs and Publications
  Discover Ethiopian Orthodox Church History
  Preaching of the week
 
  www.eotc-mkidusan.org
 
www.mahiberekidusan.org
  www.radiotewahedo.org
  www.tewahedomedia.org
Home| Feedback| Webmaster
EOTC-DC Diocese., All Rights Reserved