:::ዜናዎች:::

:::ያግኙን :::

ርዕሰ አንቀጽ

ወጣቱ ወዴት ነው መሄድ ያለበት)
የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በሃይማኖት ፍቅር በነደዱ፣ ለተጋድሎ ራሳቸውን በሰጡ የአባቶቻቸውን ታሪክ ለመድገም በቆረጡ ታሪክ ሠሪ ወጣቶች የተሞላ ነው፡፡ እነ አቤልን፣ እነ ይስሐቅን፣ እነ ያዕቆብን፣ ነቢዩ ዳንኤልን እና ሠለስቱ ደቂቅን፣ ባሮክን እና አቤሜሌክን በብሉይ ኪዳን እናገኛቸዋለን፡፡
ተጨማሪ

 
 
  ራእይ
 
የጥያቄዎ መልስ
  ሊቀ ጳጳሱን ይጠይቁ
 
 

መኑ አንተ? አንተ ማነህ?

 የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በሃይማኖት ለወለደቻቸዉ  ልጆቿ ብቻ ሳትወሰን  ለኢትዮጵያዉያን ወገኖቿ ሁሉ የመጀመሪያዉን ትምህርት ቤት በመክፈት ሥነ ጽሑፍን[፣ ሥነ ጥበብን፣ ሥነ ስዕልን፣ አስተዳደርን፣ በብቃትና  በትጋት አስተምራለች። ከዚህም ጋር በጋራ የአገር ድንበር መጠበቅን፣ በሀዘን በደስታ ተባብሮና ተደጋግፎ መኖርን፣ ለትዉልድ ሁሉ አበርክታለች።  አበዉ እንደሚሉት ታሪክ ትልቅ ትምህርት ቤት ከመሆኑም በላይ መስተዋት ነዉና ከመልካም ታሪኳ እንደተማርነዉና እንደተረዳነዉ እዉነተኛ ልጆቿን ለይታ የምታዉቅ በመሆኗ መልካም ስምን ሰጥታ ሞግስን እና ክብርን አጎናጽፋ ትልቅ ትንሽ፣ ነጭ ጥቁር፣ ሩቅ ቅርብ፣ ዘመድ ባዕድ ሳትለይ እናትነቷን አዉቀዉ፣ ጥሪዋን ሰምተዉ፣ ሥራቷን ተቀብለዉ፣ ሕጓን አክብረዉ ለሚመላለሱት ሁሉ አድልዎ በሌለበት የእናትነት ፍቅሯ የማይጠፋ የዘለዓለም ስምና ክብር ከድል አክሊል ጋር አቀዳጅታለች። አገራችን ኢትዮጵያ የአኩሪ ታሪክ ባለቤት ለመሆን ካበቃትም ምክንያት አንዱና ዋናዉ ሀገረ እግዚአብሔር መሆኗ ነዉ። ጥንትም በዘመነ ብሉይ በኋላም በዘመነ ሐዲስ ከእግዚአብሔር ያልተለየች አገር ስለሆነች ልጆቿን በፈሪሃ እግዚአብሔር፣ በሃይማኖት፤ በጥበብ፣ በእንግዳ ተቀባይነት፣ በወገን ወዳድነት አሳድጋለች።

በአንጻሩም ወይቤሎ ካልዕየ እፎ ቦእከ  ዝየ ዘእንበለ ትልበስ ልበሰ መርዓ ወተፈጽመ ውእቱ   ማቴ ፳፪ ፲፪  ወዳጄ ሆይ የሰርግ ልብስ ሳትለብስ እንዴት ወደዚህ ገባህ? አለዉ እርሱም ዝም አለ በማት ፈጣሪዋ  በአስተማራት መሠረት  የሃይማኖት ካባ ለብሰዉ፣ ሥርዓቷንና ሕጓን ጥሰዉ፣ አንድነቷን ለማፍረስና ሃይማኖቷን ለመለወጥ ተዛዝኖና ተባብሮ በሚኖረዉ ሕዝቧ ላይ ጥላቻን ለማንገሥ በመምሰል የሚገቡትን ሐሰተኞች አንተ ማነህ? እናንተስ እነማን ናችሁ? እያለች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ማንነታቸዉን በአደባባይ እያሳየች ልጆቿ ሃይማኖታቸዉንና አንድነታቸዉን ጠብቀዉ እንዲኖሩ አስተምራለች። ኃላፊነቷንም ተወጥታለች። ከታሪክ ማኅደር እንደምንረዳዉ የቤተ ክርስቲያን ድምጽ ድምጻቸዉ ከሆኑ ነገሥታት አንዱ ዐፄ ገላዉዴዎስ አባ ቤርሙዴዝ የተባለ ካቶሊካዊ የኢትዮጵያ ጳጳስ እኔ እንድሆን ከሮማዉ ጳጳስ አስፈቅጃለሁና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በሮም ቤተ ክርስቲያን በታች እንድትሆን ከዓፄ ልብነ ድንግል ተዋዉለን ነበርና አሁንም እንደዉላችን የቤተ ክህነቱን ሹመት ልቀበል ብሎ ቢአመለክት እኔ እንደዚህ ያለዉን አላዉቅም። እርዳታ ስለአደረጋችሁልኝ ዋጋችሁን በተቻለኝ እመልሳለሁ። ኢትዮጵያን የወደደ እዚሁ ኢትዮጵያዊዉን መስሎ ይቆይ ይቀመጥ። አልቀመጥም ያለ ዋጋዉን  እየተቀበለ  ይሂድ።  በሀገሬ ላይ ሁለተኛ የዉጭ ሰንደቅ አላማ ተተክሎ እንዳላይ ብለዉ ስለአዘዙ ----አባ ቤርሙዴዝ ወደ ሀገሩ ከሄደ በኋላ የኢትዮጵያ ሕዝብ እግዚአብሔርን አክባሪና እንግዳ ተቀባይ መሆኑን ተናገገረ። የኢትዮጵያ ሕዝብ መንፈሳዊ ሥራ ስለሚወድ መንፈሳዉያን መስለን የመነኩሴ ልብስ ለብሰን መስቀልና መጽሐፍ ይዘን ሄደን ሕዝቡንና ንጉሱን እየበጠበጥን እርስ በርሱ እየተፋጀ ሕዝቡ ሲቀነስ መንግሥቱ ሲኮስስ ጠብቀን በጦር ኃይል አገሩን አጥፍተን እንገባና ቅኝ አገር አድርገን እንጠቀምበታለን ብለዉ አሰቡ። በዚህ አኳኋን የኢትዮጵያን ሕዝብ እርስ በርሱ እንዳፋጁ አራት መቶ ዘመን መሆኑ ነዉ በማለት አቶ አስረስ የኔሰዉ የተባሉት ታሪክ ጸሐፊ ትቤ አክሱም መኑ አንተ በተባለዉ መጽሐፋቸዉ በኢትዮጵያና  በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ላይ የነበረዉን ወረራ ገልጸዉታል። ከዚህ ታሪክ ልናስተዉለዉ የሚገባን ሰዎች በደካማ ጎን ገብተዉ ድብቅ ዓላማቸዉን ለማሳካት የሚአደርጉትን ጥረት ጠንቅቆ በማወቅ ማነህ አንተ?  እንዲህ አይነቱንስ ሥርዓት ከየት አመጣህዉ? ማለቱ መልካም የሃይማኖትና የታሪክ ዉርስ መሆኑን ነው።

ስለ ቤተ ክርስቲያናችን ታሪክ ከዚህ በላይ በመጠኑ ካስታወስን ዛሬስ ከእኛ ምን ይጠበቃል? ማነኝ? እኔ ምን እየሰራሁ ነዉ?  ማነህ? አንተ ምን እየሠራህ ነዉ? ተባብለን ባለመጠያየቃቸን  ሁላችንም  እንደመሰለን  በየአቅጣጫችን በመሄዳችን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በአለንበት አገር ቀዛፊ የሌላት መርከብ መስላለች። በዚህም ፈታኝ ወቅት የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች የሆንን ሁሉ ራሳችንን በመመርመር ኃላፊነታችንን እንድንወጣ አደራ ካለብን አበዉ ካህናት አኃዉ ዲያቆናት ቤተ ክርስቲያን ብዙ  ትጠብቃለች። እንደሚታወቀዉ ካህናት ሕዝቡን በእዉነተኛዋና የኖኅ መርከብ ምሳሌዋ በሆነችዉ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን አሳፍረን ወደ ወደቧ ሰማያዊት ኢየሩሳሌም የማድረስ ሥልጣን የተሰጠን መሆናችን በቅዱሳት መጻሕፍት የተረጋገጠ ነዉ። በመርከቧ ዉስጥ ልዩ  ጠባይ፤ልዩ ቋንቋ፤ ልዩ ባህል፤ልዩ  ዕዉቀት፤ልዩ  መልክ ፤ያላቸዉ ወገኖች የሚሳፈሩ ሲሆን ወደ መርከቧ ከተሳፈሩ በኋላ ግን ልዩነቱ ጠፍቶ የሰው ልጅ መነሻዉ  አንድ እንደሆነ ሁሉ መድረሻዉም  በሃይማኖት  አንድ ነው። የሰው ልጆች ሁሉ በፍቅርና በሰላም ከዓለም ጥፋት በሚድኑባት መርከብ አሳፍሮ ወደ ወደቡ ለማድረስ ደግሞ ጽኑዕ ሃይማኖት፤ እዉነተኛ ፍቅር፤ ትዕግስት፤ ዓላማን ማወቅ፣ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት መመራትን ይጠይቃል።

ማእበሉን ተቋቁሞ የተለያየዉን በሃይማኖት አንድ አድርጎ ወደ ሚፈለገዉ ወደብ ማድረስ የሚቻለዉ በመርከቧ ዉስጥ ኃላፊነት ተሰጥቶን የተቀመጥን ካህናት ተግባብተን፤ ተስማምተን የቤተ ክርስቲያንን ቀኖና ጠብቀን ፤በሕገ ቤተ ክርስቲያን ተገዝተን፤ መጓዝ ስንችል ብቻ ነዉ። እኛ ሳንግባባ ፤ ምእመናንን ማግባባት፣ እኛ ሳንስማማ ተስማሙ ማለት፣ እኛ ያፈረስነዉን ሕግና ሥርዓት ምእመናንን ጠብቁ ማለት፣ እኛ ያላደረግነዉን ከሌላዉ መጠበቅ፣ በራሱ ኃላፊነታችንን ከግምት ዉስጥ ይጥለዋል። ከዚህም የተነሳ አማናዊቷ መርከብ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን በአገልጋዮቿ አለመግባባት እና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን አለመጠበቅ ጸላኢ ያስነሳዉ የፈተና ማዕበል እያናወጣት ትገኛለች። የዚህም ምክንያት አንዳንዶቻችን የተጠራንበትን ዓላማ አዉቀን የአባቶቻችንን ፈለግ ተከትለን ማዕበሉ ከሚያመጣዉ ጥፋት ተሳፋሪዎችን ለማዳን በተሰጠን መክሊት ለማትረፍ ስንታገል፤ አንዳንዶች ድግሞ መርከቡን ወደጎን ትተዉ የራሳቸዉን ጀልባ ሠርተዉ መሰሎቻቸዉን አሳፍረዉ ሲጓዙ ይታያሉ። ሌሎቻችን ደግሞ ከመርከቧ ክፍል የተወሰነዉን ከልለን ሥልጣን የተሰጣቸዉ የመርከቡ  ጠባቂዎችና ኃላፊዎች የማይከታተሉትና የማይገቡበት ወሰን አዘጋጅተናል። ከዚህም ሌላ ጥቂቶች ደግሞ መርከቧ ምእመናንን ከጥፋት ጠብቃ  ወደ ወደቡ እንድታደርስ ሳይሆን የነርሱን ፍላጎት እንድታሟላ ወደ ሚፈልጉት አቅጣጫ እንድትጓዝ ሊቀዝፉ ሲታገሉ ይታያሉ።

ይህ ሁሉ መጓተት የመርከቧን የጉዞ አቅጣጫ ባያስቀይራትም መርከቧ መሄድ ባለባት ፍጥነት እንዳትጓዝ፤ በዘመኑ ያለነዉም አገልጋዮቿ ክብር እንዳናገኝ፤ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ምእመናን እንዲደናገሩ፤ የታሪክ ተወቃሽም እንድንሆን ከመጋበዙም በላይ፤የሃይማኖታችን ተቃዋሚዎች አጋጣሚዉን እንዲጠቀሙ አድርጓቸዋል።

ስለዚህ ለቤተ ክርስቲያን ዕድገት የተጠራንና የተሰየምን ካህናት በጉዳዩ ላይ ይበልጥ ልናስብበት ይገባል። በመጀመሪያ ደረጃ ካህናት የተለያዩ መዐርጋት ልናገኝ የቻልነዉ በዘር በሐረግ ሳይሆን በፈቃደ እግዚእብሔር በቤተ ክርስቲያን ህልዉና ነዉ። ስለሆነም ከማንኛዉም ነገር በላይ ለመንጋዉና ለቤተ  ክርስቲያን ሙሉ ሕይዎታችችንን ልንሰጥ ይገባል። ላከበረንና ለመረጠንም ለቤተ ክርስቲያን አምላክ ልንታዘዝ ይገባል። በመሠረቱ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን ባይመሠርታትና ቅዱሳን ሐዋርያትን ባይሾም  ቅዱስ ሲኖዶስ ባልነበረ፣ ሊቃነ ጳጳሳት ባይኖሩ ካህናት ዲያቆናት ባልነበሩ፣ ካህናት ዲያቆናት ባይኖሩ ምእመናን ባልነበሩ። የሁሉም መኖርና ህልዉና የተረጋገጠዉና  የሚረጋገጠዉ ቤተ ክርስቲያንን በደሙ ከመሠረታት ከአምላካችንና ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ተነስተን ሰንሰለቱ ሳይበጠስ ሥርዓቱ ሳይፈርስ ከአለንበት ዘመን ስንደርስና ወደፊትም ስንጓዝ ብቻ ነዉ። በአጠቃላይ ከግንዱ የተለየ ቅርንጫፍ ልምላሜ እንደሌለዉ ሁሉ ከቅዱስ ሲኖዶስ የተለየች በሀገረ ስብከት ያልታቀፈች ወይም ያልተመሠረተች ቤተ ክርስቲያን በስም አጠራር ብቻ ራሷን ያከበረች በግብር ግን የተለየች በተዛዋሪ መልኩ የዘመኑን ክርስትና የተቀበለች ያሰኛታል።

እንደሚታወቀዉ የአብያተ ክርስቲያናትን አስተዳደር በተመለከተ በዓለም ዙሪያ ሁለት ዓይነት አስተዳደር እንዳለ እንገነዘባለን። አንደኛዉ እርከናዊ ሲሆን ሁለተኛዉ ደግሞ ክፍፍላዊ በመባል ይታወቃል። እርከናዉያን የሚባሉት ጥንታዉያን አብያተ ከርስቲያናት ሲሆኑ እነርሱም  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ  ቤተ ክርስቲያን፤ የግብፅ፤  የአርመን፤ የሶርያ፤ የሕንድ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት በአንጻሩም የግሪክ የሮም እና የመሳሰሉት ሲሆኑ በአንድ የበታች አካል ሃይማኖታዊ ወይም አስተዳደራዊ ችግር ቢፈጠር ወይም ቢነሳ ጉዳዩ የሚታየዉ ከላይ ባለዉ አስተዳደራዊ መዋቅር ይሆናል። በማንኛዉም ጊዜ የበላዩ ክፍል የሚሰጠዉ ዉሳኔ ደረጃዉን ጠብቆ ይግባኝ ከመጠየቅ በስተቀር  ተግባራዊ ይሆናል።  ክፍፍላዉያን የሚባሉት ደግሞ በአብዛኛዉ የፕሮቴስታንት ክፍሎች ናቸዉ። በዚህ የአስተዳደር ስልት  በመካከላቸዉ አንድ ችግር ቢፈጠር ጉዳዩ ወደ ሕዝቡ ወርዶ ሕዝቡ በሚሰጠዉ አስተያየትና በድምጽ ብልጫ ይወሰናል።ይህም የአስተዳደር ስልት ክፍልፋይ እምነቶችን ከማብዛቱም በላይ ሕዝብን ከሕዝብ የሚአለያዩ ራስ ወዳዶችን ፈጥሮአል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከላይ እንደተገለጸዉ በአንደኛ ደረጃ የተጠቀሰዉን አስተዳደር በመከተል ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን መዋቅር ያላት ናት። በዉጭ ዓለማት የሚገኙ በስሟ ከቤተ ክርስቲያኗ ፈቃድ ሳያገኙ ራሳቸዉን ያደራጁ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ከአስተዳደር መረቧ ወጥተዉ ሁለተኛዉን የአስተዳደር ስልት ተከትለዉ የማይገባዉን ሥራ ሲሥሩ ይታያል። ይህንንም ጉዳይ በንጹሕ ሕሊና ለተመለከተዉ የቤተ ክርስቲያኒቱን ታሪክ፤ የአባቶቻችንን ማስተዋል ወደኋላ መለስ ብሎ ካለመቃኘት የተነሣ የመጣ ስሕተት መሆኑን ያስረዳል።

አባቶቻችን እና እናቶቻችን ይችን ቤተ ክርስቲያን በአንድነቷ እንደጸናች ከሙሉ ክብሯ እና ሥርዓቷ ጋር ሲአስረክቡን ሁሉም ነገር ተመችቷቸዉ አልነበረም። በተለያዩ ጊዜያት  አንድ መቶ አሥራ አንድ ጳጳሳትን ቤተ ክርስቲያን እንዳትዘጋ ከግብፅ ለማስመጣት  የአንበሳ ደቦል የዝሆን ግልገል ይዘዉ፣ የወርቅ ቡችላ የዝሆን ጥርስ ጭነዉ፣ በመገበር ከሺ በላይ የተቆጠሩትን ዘመናት ሲአሳልፉ ለሀገሩ እንግዳ ለቋንቋዉ ባዕድ የሆኑትን ጳጳሳት በአባትነት ተቀብለዉ ሲመሩ መኖራቸዉ፣ ሞኝነት ወይም አላዋቂነት ሳይሆን አዋቂነትና ብልህነት ነበረ።ይህም የሚታወቀዉ ጸሎታቸዉና ድካማቸዉ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት  አግኝቶ ቤተ ክርስቲያን በራሷ ልጆች እንድትመራ አስችሏታል።

ስለዚህ ወገኖቼ እንደ አባቶቻችን ብልሆች ሆነን ዛሬ እኛ ያዛባነዉን እኛዉ ልናስተካክለዉ ይገባል። የለያየነዉን አንድ ልናደርገዉ ይገባል። ይህን ሳናደርግ ብንቀር ደግሞ የነገዉ ተተኪ ትዉልድ አንድም የአባቶቹን ሳይሆን የአያቶቹን የቅድመ አያቶቹን ታሪክ፣ ያላቸዉን እምነትና ፍቅር በማወቅ ሲወቅሰን ሲከሰን ይኖራል።በሌላ መልኩም  ታሪኩን ሳያዉቅ ዘመኑን መስሎ በከንቱ ታሪክ የለሽ ሆኖ ይኖራል። በዚያም አለ በዚህ ከተወቃሽነት አንድንም። ስለሆነም ችግሩ እየሰፋና እየባሰ ሄዶ ለመፍታት ከማስቸገሩ በፊት ጊዜዉ ዛሬ ነዉና መፍትሔ እንፈልግለት። ለወደፊቱም ከቤተ ከርስቲያን ሥርዓት ዉጭ በግል ፍላጎታቸዉ ያለ ሊቀ ጳጳሱ ቡራኬ ቤተ ክርስቲያን ከፍተናል የሚሉ ሁሉ ሥርዓታችን አለመሆኑን ተረድተዉ ሊያቆሙ ይገባል።

በዘጠና አራተኛዉ የባስልዮስ አንቀጽ እንዲሁም በፍትሕ መንፈሣዊ ዐንቀጽ ፫ እንደተገለጠዉ ወኢይሕንጹ ቤተ ክርስቲያን ዘእንበለ በትእዛዘ ኤጲስ ቆጶስ ወለእመ ተሀበለ ፩ዱሂ ወገብረ ካልአ እምዝንቱ ኢይቅረብ ቁርባነ በዉስቴታ እስከ ዘለዓለም ወለእመ ተሀበለ ካህን ዘንተ ወቀረበ በዉስቴታ ቁርባነ ይትመተር ያለ ኤጲስ ቆጶሱ ትእዛዝ ቤተ ክርስቲያንን አይሥሩ፣ አንድ ስንኳ ደፍሮ ከዚህ ዉጭ ቢሠራ በዉስጧ እስከ ዘለዓለም ቁርባንን አይቁረብ፣ ቄሱም ይህን ተላልፎ ቁርባንን ቢቆርብ ይሻር።በማለት ስለ ቤተ ክርስቲያን አመሠራረት እየተናገረ ሰምተዉ እንዳልሰሙ አዉቀዉ እንዳላወቁ በድፍረት የሚመላለሱትን ሁሉ ሥርዓታችን አይደለምና አቁሙ ልንላቸዉ ይገባል።

በአጠቃላይ የቤተ ክርስቲያናችንን ሥርዓትና ቀኖና መሪ አድርገን፣ የነበረዉንና ሊኖር የሚገባዉን ሕገ ቤተ ክርስቲያን ጠብቀን፣ መልኩን የቀየረ በስም የከበረ ሲገጥመን አንተ ማነህ? እናተስ እነማናችሁ? እያልን የቤተ ክርስቲያናችንን አንድነት ልንጠብቅ ካልቻልን ተጠያቂዎች እኛዉ እንዳንሆን ነቅተን ተግተን እንጠብቅ።

የዚህም ዐዉደ ርዕይ አንዱ ዓላማ ቤተ ክርስቲያኒቱ የነበራትንና ያላትን ወደፊትም ሊኖራት የሚገባዉን ለማስጨበጥና ለማስዳሰስ በሚያስችል መልኩ ማዘጋጀት ነው። በተጨማሪም ትዉልዱ አንድነቱን ጠብቆ የሚጓዝበትን መንገድ አዉቆ የአባቶቹን አደራ እንዲጠብቅ ራሱን እንዲያድን በታሪክ መስተዋትነት የረቀቀዉን አጉልቶ የራቀዉን አቅርቦ የማሳየት ብቃት ያለዉ ዐዉደ ርዕይ ነዉ። በመሆኑም አዘጋጁ ክፍል ማኅበረ ቅዱሳን፣ በዉስጡም ኃላፊነታቸዉን የተወጡ የየክፍሉ ሠራተኞች ሊመሰገኑ ይገባቸዋል። ይበልጥም እንዲሠሩ ማበረታቻ ያስፈልጋቸዋል። በአለንበት ዘመን ታሪክ ጠባቂ ሆኖ ከመገኘትም ጋር የታሪክ አስተማሪ ሆኖ መገኘት ታላቅ ስጦታ ነዉ። ይልቁንም ያለንበት አገር ዉጣ ዉረድ የበዛበት፣ በወዝህ ጥረህ ግረህ ብላ የሚለዉ ቃል የሚተገበርበት፣ ኑሮን ለማሸነፍ ደፋ ቀና የሚባልበት፣ በቂ የእረፍት ጊዜ የማይገኝበት ሲሆን መስዋዕትነት በመክፈል ለተደረገዉ ሙሉ ዝግጅት ትኩረት  መሠጠት መንፈሣዊ ግዴታችን መሆን አለበት።

በአጠቃላይ የቤተ ክርስቲያንን አንድነት ለመጠበቅ፣ ምእመናን በታሪካቸዉና በይዞታቸዉ መንፈሣዊ ኩራት እንዲኖራቸዉ፣ በማሕበራዊ ኑሮአቸዉና በአንድነታቸዉ ልዩነት እንዳይፈጠር፣ በሃይማኖታቸዉ እንዲጸኑ፣ የአባቶቻቸዉን አደራ ጠብቀዉ ለልጆቻቸዉ እንዲያወርሱ ከማስገንዘቡም በላይ በቃልም፣ በጽሑፍም፣ በዕይታም አስተማሪ ሆኖ በመቅረቡ በስመ እግዚአብሔር እናመሰግናለን።

                                    አባ አብርሃም
 
ሊቀ ጳጳስ
ሐምሌ ፲፭/ ፳፻ ዓም

Home| Feedback| Webmaster
EOTC-DC Diocese., All Rights Reserved