:::ዜናዎች:::

:::ያግኙን :::

ርዕሰ አንቀጽ

ወጣቱ ወዴት ነው መሄድ ያለበት)
የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በሃይማኖት ፍቅር በነደዱ፣ ለተጋድሎ ራሳቸውን በሰጡ የአባቶቻቸውን ታሪክ ለመድገም በቆረጡ ታሪክ ሠሪ ወጣቶች የተሞላ ነው፡፡ እነ አቤልን፣ እነ ይስሐቅን፣ እነ ያዕቆብን፣ ነቢዩ ዳንኤልን እና ሠለስቱ ደቂቅን፣ ባሮክን እና አቤሜሌክን በብሉይ ኪዳን እናገኛቸዋለን፡፡
ተጨማሪ

 
 
  ራእይ
 
የጥያቄዎ መልስ
  ሊቀ ጳጳሱን ይጠይቁ
 
 

አሐቲ

ወነአምን በአሐቲ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንተ ላዕለ ኩሉ ጉባኤ እንተ ሐዋርያት፣ የሐዋርያት ጉባኤ በምትሆን፣ከሁሉም በላይ በሆነች በንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እናምናለን በማለት በቁስጥንጥንያ የሰበሰቡ 150 አባቶች እንደ መሠከሩት ስለ ቤተ ክርስቲያን ስንናገር አራቱ ነገሮች ማለትም አንዲት፣ ቅድስት፣ከሁሉም በላይ የሆነች፣ ሐዋርያዊት የሚሉትን መመስከር አለብን።

ቅድስት ስንል  ቅዱስ በሆነው የክርስቶስ ደም የተዋጀች ቤተ ክርስቲያን ወደ እርስዋ የመጡትን ሁሉ የምትቀድስ ቅድስት ናት ማለታችን ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን በማለት እንደመሰከረው ቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔር በደሙ የዋጃት ቅድስት ቤት ናት።  በሃይማኖት ወደ እርስዋ የመጡትን ሁሉ ትቀድሳለች እንጂ እርስዋን ማንም ሊያረክሳት አይቻለውም።

ጉባኤ ቁስጥንጥንያ በተካሄደበት በቁስጥንጥንያ ከተማ የምትገኘው ጥንታዊቷ ሀጊያ ሶፊያ ቤተ ክርስቲያን

ከሁሉም በላይ ናት ስንልም በቤተ ክርስቲያን የተሾሙ ሁሉም እርስዋን ለማገልገል፣ ለእርስዋ ራሳቸውን ለመስጠት፣ ለእርስዋ ለመሠዋት ተሰየሙ እንጂ ከቤተ ክርስቲያን በላይ ማንም የለም፡፡ ከፓትርያርክ እስከ ምእመን በርስዋ ተሰየሙ፣እርስዋንም ሊያገለግሉ ተሰየሙ እንጂ ከእርስዋ በላይ አልተሰየሙም። ቤተ ክርስቲያን ከሌለች ሁሉም ይኖሩምና፡፡ ለእርስዋ ሕይወታውን ይሰጣሉ። በሌላም በኩል ደግሞ ቤተ ክርስቲያን የሁሉም ናት ማለታችን ነው። ሮማዊም፣አይሁዳዊም፣የግሪክም ሰው ቢሆን ወደ እርስዋ በሃይማኖት እስከ መጣ ድረስ ወደ ውጭ አታወጣውም። የነ እገሌ ናት እንጂ የነ እገሌ አይደለችም አትባልም።

ሐዋርያዊት ናት ማለታችንም በሐዋርያት ምስክርነት፣ ትምህርት፣ ትውፊት እና ሥልጣነ ክህነት የምታምን እና የምትመራ ናት ማለታችን ነው።

አንዲት ስንል ደግሞ ቤተ ክርስቲያን ራስዋ አንድ ክርስቶስ በመሆኑ/ኤፌ. 5፥23/እርስዋም አካሉ ናትና አንዲት ናት። ሃይማኖት አንዲት ናትና/ኤፌ.4፥5/። ይህቺ ሃይማኖት የምትመሰከርባት ቤተ ክርስቲያንም አንዲት ናት ማለታችን ነው።

በዚህ ጽሑፍ አንዲት ናት በሚለው ምስክርነት ላይ እናተኩራለን።

ስለ ቤተ ክርስቲያን አንድነት ስንናገር በአራት ነገሮች ስላላት አንድነት መናገራችን ነው። እነዚህም፡

1.        በመሠረተ እምነት/በዶግማ/

2.       በሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን /በቀኖና/

3.       በትውፊት

                   4.     በአስተዳደር

1.                   በመሠረተ እምነት/ በዶግማ/

ቤተ ክርስቲያን ከቅዱስ ሲኖዶስ እስከ ምእመናን ድረስ ባለው መዋቅርዋ ሁሉ የምትመሠክረው እምነት ከቀደሙት አበው እምነት፣ ከቅዱሳት መጻሕፍት ምስክርነት ያልተለየ ከሆነ አንድነትዋ ተጠብቆ ይኖራል። እያንዳንድዋ አጥቢያ ከቤተ ክርስቲያን መሠረተ እምነት በምንም መልኩ መለየት የለባትም። በመሠረተ እምነት ጉዳይ ክርክር ቢነሣ የቅዱሳት መጻሕፍትን ምስክርነት፣የአበውን ትምህርት  መሠረት አድርጎ  የመጨረሻ ውሳኔ መስጠት ያለበት ቅዱስ ሲኖዶስ ብቻ ነው። ከቅዱስ ፓትርያርኩ እስከ ምእመናኑ ድረስ ያሉት ሁሉ ይህንን ርቱዕ እምነት የመጠበቅ እና የማስጠበቅ፣ቤተ ክርስቲያንንም ከመናፍቃን እና ከቀሳጥያን የመጠበቅ ግዴታ አለባቸው።

 አንድ ሰው ከቤተ ክርስቲያን ትምህርት የተለየ ትምህርት የሚያስተምር፣የተለየም እምነት የሚያምን ከሆነ ከቤተ ክርስቲያን አንድነት የወጣ ይሆናል። አበው ሐዋርያት በመክንዮአቸው እኛስ የሃይማኖት ለዋጮችን ሥራውን እንጸየፋለን ፣ሕግ መለወጣቸውንም በማለት እንዳስተማሩን ሃይማኖትን በምግባር መግለጥ እንጂ መለወጥ ክርስቲያናዊ ተግባር አይደለም። ይህንንም የሚያደርግ ቢኖር ይመከራል፣ወደ ቤተ ክርስቲያን አንድነት ይመለስ ዘንድ ዕድል ይሰጠዋል፣ እምቢ ካለም ተወግዞ ይለያል። ይህም በአርዮስ፣ በመቅዶንዮስ፣ በንስጥሮስ ታሪክ ታውቋል።

2.                 በሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን/በቀኖና/

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሁሉ በአግባብ እና በሥርዐት ይሁን/1ኛ ቆሮ. 15፥40/ በማለት ባስተማረው መሠረት ቤተ ክርስቲያን አምልኮዋን የምትፈጽመበት ሥርዐት አላት። ይህም ሥርዐት አባቶች እና ምእመናን አንድ ሆነው  ባንዲት ሃይማኖት እንዲኖሩ ለማድረግ የሚደነገግ መጽሐፋዊ ሕግ ነው። በዚህ ቤተ ክርስቲያናዊ ሕግ እስከተመራን ድረስ ሁላችንም በአንድ ልብ ሆነን እግዚአብሔርን እናገለግላለን። ይህም ሥርዐት ቅዱሳት መጻሕፍትን መሠረት አድርጎ ከሐዋርያት ዘመን ጀምሮ በተነሡ አበው ተደንግጎ በቅዱስ ሲኖዶስ የጸና ነው። ይህንን ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን የመሥራት ሥልጣን የተሰጠው ለቅዱስ ሲኖዶስ መሆኑን ሐዋርያት በሲኖዶሳቸው በዐንቀጽ 31 ከፍርድ ወገን እኛ ያጎደልነው ቢኖር  በሚገባ እናንተ ፍረዱ፣ በሁላችንም መንፈስ ቅዱስ አድሮብናልና ብለዋል።

3.                 በትውፊት

አስቀድሞ ቅዱስ ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ክርስቲያኖች በቃላችንም ቢሆን ወይንም በመልእክታችን የተማራችሁትን ትውፊት ያዙ በማለት እንዳስተማረው/2ኛተሰ.2፥15/ ሐዋርያዊ የሆነውን የቤተ ክርስቲያን ትውፊት መጠበቅ ቤተ ክርስቲያን በአሠራርዋ እና በባሕልዋ አንድ ሆና እንድትኖር ያደርጋታል፡፡ ለምሳሌ የዘመን አቆጣጠርዋ አንድ በመሆኑ የበዐላት እና የአጽዋማት ቀኖናዋ ተጠብቆ እንዲኖር አድርጓታል።

4.                 አስተዳደር

    የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ስንል ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ድረስ ያለው ባንድ በኩል፣እያንዳንዱዋ አጥቢያ እርስ በርስዋ ያላትን ግንኙነት የሚወስነውን በሌላ ወገን ማለታችን ነው። በዚህ መዋቅር ውስጥ ሁለት ዐይነት ተዋረዶች አሉ። ክህነታዊ እና መዋቅራዊ።

    ክህነታዊ የምንለው ከፓትርያርክ እስከ ዲያቆን ያለውን ነው። ቅዱስ ሲኖዶስ ጳጳሳትን ይሾማል፣ ጳጳሳትም ካህናትን ይሾማሉ፣ ካህናትም ምእመናንን ያጠምቃሉ። ቅዱስ ሲኖዶስ ከሌለ ጳጳሳት፣ ጳጳሳት ከሌሉም ካህናት፣ ካህናትም ከሌሉ ምእመናን አይኖሩም።

 

   

አንዲት ቤተ ክርስቲያን ክህነታዊው አንድነትዋ እንዲጠበቅ ሐዋርያዊ ቅብብል ያስፈልጋታል። ሐዋርያዊ ቅብብል ማለት ከሐዋርያት ጀምሮ ያለ መቋረጥ የሚመጣ ክህነታዊ ቅብብል ማለት ነው። ሐዋርያት ሐዋርያውያን አበውን ሾሙ፣ ሐዋርያውያን አበውም ሌሎች አበውን ሾሙ፣ እንደዚህ እያለ የሲመት ቅብብሉም ሳይቋረጥ ከኛ ዘመን ደርሶል። ለምሳሌ ቅዱስ ማርቆስ አንያኖስን ሾመ፣ አንያኖስም ቀጣዩን አባት ሾመ፣ እንዲህ እያለ ከሃያኛው ፓትርያርክ ከአትናቴዎስ ዘንድ ደረሰ። ከሣቴ ብርሃን ሰላማም ከአትናቴዎስ ተሾሞ መጣ። አባ ሰላማም ካህናትን ሾመ።

  የእስክንድርያ ሲኖዶስ የመጀመርያዎቹን ኢትዮጵያውያን ጳጳሳት ሾመ፣ ከነዚያ ጳጳሳት መካከልም ብጹዕ  ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስን ፓትርያርክ አድርጎ ሾመ፣ ከዚያ በኋላም ቅዱስ ሲኖዶስ ጳጳሳትን ሾሟል፣ወደፊትም ይሾማል። ይህም ሐዋርያዊው ቅብብል ሳይቋረጥ ከኛ ዘንድ መድረሱን ያሳያል። ይህ ቅብብል የሚቋረጠው እንደ አርዮስ ሲወገዙ ወይንም እንደ ይሁዳ በፈቃዳቸው ሲተዋት  ነው።

ለምሳሌ አርዮስ በኒቂያ ጉባኤ ስለተወገዘ ሐዋርያዊ ሹመቱ ከርሱ ተወስዳለች። ስለዚህ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያንን መፈጸም አይችልም። በሌላም በኩል ደግሞ በዚህ ሀገር የሚገኙ ፕሮቴስታንቶች በፈቃዳቸው ሲመትዋን  ትተዋታልና ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያንን መፈጸም አይችሉም። በውጭው ዓለም ተቀምጠው ሕገ ወጥ ሲኖዶስ በማቋቋም የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት እና ሥርዓት የጣሱትን አንድነቷንም የተፈታተኑትን መናፍቃንን በተመለከተ ጥር 25 ቀን 1999 ዓም የተላለፈው የቅዱስ ሲኖዶስ ውግዘት የመናፍቃኑን ክህነት በማንሣቱ ከሐዋርያዊ ቅብብል ውጭ ሆነዋል። በመሆኑም የሚፈጽሟው ማናቸውም ክህነታዊ ተግባራት /ማጥመቅ፣ መናዘዝ፣ ማቁረብ፣ ክህነት መስጠት፣ ወዘተ ሁሉ ሕጋዊ አይደለም ማለት ነው።

ይህ ክህነታዊ መዋቅር ተጠብቆላት የማይኖር ቤተ ክርስቲያን ቤተ ክርስቲያን ናት ለማለት አይቻልም። ድርጅት ትሆናለች እንጂ።

ሁለተኛው ተዋረድ ደግሞ መዋቅራዊ ተዋረድ ነው። ይህ መዋቅራዊ ተዋረድም ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን የሚደርስ መዋቅር ነው። መንበረ ፓትርያርክ ማለት ቅዱስ ፓትርያርኩ የሚቀመጡበት፣ ሲኖዶሱ የሚሰበሰብበት፣ የቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ ሥራ በበላይነት የሚከናወንበት ነው። በፍትሐ ነገሥት  ዐንቀጽ 4 መሠረት ጳጳሳት በየጊዜው ቅዱስ ፓትርያርኩ ባሉበት በመንበረ ፓትርያርኩ ተሰብስበው ስለ ቤተ ክርስቲያን ጉዳይ እንዲመክሩ ያዝዛል።

ከመንበረ ፓትርያርኩ በታች የሀገረ ስብከት መኖር የግድ ነው። ይሄውም ዓለምን ዕጣ በዕጣ ተካፍለው በመውጣት የመጀመርያዎቹን አህጉረ ስብከት ከመሠረቱት ከሐዋርያት ጀምሮ የተመሠረተ ነው። በፍትሐ ነገሥት ዐንቀጽ 5 ቁ. 156 ጀምሮ እንደተገለጠው ኤጲስ ቆጶሳት የሚሾሙበት ሀገረ ስብከት ያስፈልጋል። ከሀገረ ስብከትም በታች እንደየ ቤተ ክርስቲያኑ ሕግ ወረዳ፣ አውራጃ፣ ዲስትሪክት፣ ወዘተ ሊኖር ይችላል። አስገዳጅ የሆነውና የማይቀረው መዋቅር ግን አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ነው። ያለ መንበረ ፓትርያርኩ ፈቃድ ሀገረ ስብከት፣ ያለ ሀገረ ስብከትም ፈቃድ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አይቋቋምም። ፍትሐ ነገሥቱ በአንቀጽ 1 ቁ.1 ያለ ኤጲስ ቆጶሱ ትእዛዝ ቤተ ክርስቲያን አይሥሩ ይላል።  

 

ይህ አስተዳደራዊ መዋቅር ከላይ ወደ ታች/vertical/ እንዲሁም ወደ ጎን /horizontal/ የሚዘረጋ ነው። ከላይ ወደ ታች የምንለው አስቀድመን እንዳየነው ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ አጥቢያ፣ ከቅዱስ ፓትርያርኩ እስከ ምእመን የሚደርሰውን ነው። ወደ ጎን የምንለው ደግሞ በምእመናን መካከል፣ በካህናት መካከል፣ በጳጳሳት መካከል የሚኖረውን አንድነት ነው።

የምእመናን መገናኛቸው ካህናት፣ የካህናት መገናኛቸው ጳጳሳት፣ የጳጳሳት መገናኛቸው ቅዱስ ሲኖዶስ ነው። በመሆኑም ከላይ ወደ ታች ያለው መዋቅር ነው ወደ ጎን ያለውን መዋቅር ኅብረት እንዲኖረው የሚያደርገው። ይህ ከላይ ወደ ታች ያለው መዋቅር ሲፈርስ ወደ ጎን ያለን አንድነትም እንደሚፈርስ ያመለክተናል።

ወነምን በአሐቲ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እያልን በዘወትር ጸሎተ ሃይማኖትን የምንጸልይ ከሆነ የቤተ ክርስቲያን አንድነት የሚጸናባቸውን ምሶሶዎች ማጠንከር አለብን ማለት ነው። ያለበለዚያ ግን እንበለ ምግባር የሚጸለይ ጸሎት ዋጋ አልባ ይሆናል።                                       

Home| Feedback| Webmaster
EOTC-DC Diocese., All Rights Reserved