:::ዜናዎች:::

:::ያግኙን :::

ርዕሰ አንቀጽ

ወጣቱ ወዴት ነው መሄድ ያለበት)
የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በሃይማኖት ፍቅር በነደዱ፣ ለተጋድሎ ራሳቸውን በሰጡ የአባቶቻቸውን ታሪክ ለመድገም በቆረጡ ታሪክ ሠሪ ወጣቶች የተሞላ ነው፡፡ እነ አቤልን፣ እነ ይስሐቅን፣ እነ ያዕቆብን፣ ነቢዩ ዳንኤልን እና ሠለስቱ ደቂቅን፣ ባሮክን እና አቤሜሌክን በብሉይ ኪዳን እናገኛቸዋለን፡፡
ተጨማሪ

 
 
   ራእይ
 
የጥያቄዎ መልስ
  ሊቀ ጳጳሱን ይጠይቁ
 
 
 
ርዕሰ አንቀጽ

ወጣቱ ወዴት ነው መሄድ ያለበት

የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በሃይማኖት ፍቅር በነደዱ፣ ለተጋድሎ ራሳቸውን በሰጡ ፣ የአባቶቻቸውን ታሪክ ለመድገም በቆረጡ ታሪክ ሠሪ ወጣቶች የተሞላ ነው፡፡ እነ አቤልን፣ እነ ይስሐቅን፣ እነ ያዕቆብን፣ ነቢዩ ዳንኤልን እና ሠለስቱ ደቂቅን፣ ባሮክን እና አቤሜሌክን በብሉይ ኪዳን እናገኛቸዋለን፡፡ ወንጌላዊ ማርቆስ እና ዮሐንስን፣ጢ ሞቴዎስ እና ቲቶን፣ አትናቴዎስ እና ቅዱስ ጊዮርጊስን ደግሞ በሐዲስ ኪዳን ሜዳ ሲጋደሉ እናገኛለን፡፡

አስቀድሞ ጥበበኛው ሰሎሞን በጉብዝናህ ወራት ፈጣሪህን አስብ ብሎ ያስተማረው፣ የወጣትነት ጊዜ ሮጦ ለመቅደም፣ ሠርቶ ለማፍራት፣ ጨብጦ ለማጥበቅ፣ ወርውሮ ለማራቅ አመቺ የሆነ ዕድሜ ስለሆነ ነው፡፡ እሳትነት ያየለበትን ይህንን ዕድሜ ፈተናው ብዙ ነውና ሰይጣንም ለጥፋቱ ይፈልገዋል፡፡ ስሜታዊነቱ፣ ቁጣው ችኩልነቱ፣ ትዕቢቱ፣ በልዩ ልዩ ሱስ መጠመዱ፣ ፈላስፋነቱ እና ሁሉን ለእኔ ባይነቱ የሚያይልበትም ወቅት ነው፡፡

ዲያብሎስ አጥምዶ የሚሠነዝራቸውን የወጣትነት ፈተናዎች ቢቻል ሳይነኩ፣ ካልተቻለም ተቋቁሞ፣ ያም ካልሆነ ወድቆ በመነሣት ማሸነፍ የሚቻለው በእግዚአብሔር ጋሻ ውስጥ መከለል ከተቻለ ብቻ ነው፡፡ ወጣትነትን በቤተ እግዚአብሔር አገልግሎት ማሳለፍ ማለት ከእነዚህ የዲያብሎስ ፍላፃዎች ተከልሎ አስቸጋሪውን ወቅት ማለፍ ማለት ነው፡፡የወጣትነት ዕድሜ የሚያጎናጽፋቸውን ኃይልን፣ ዕውቀትን፣ ትጋትን፣ አትንኩኝ ባይነትን፣

አልሸነፍ ባይነትን ለጽድቅም ለኃጢአትም ማዋል ይቻላል፡፡ ዋናው አጠቃቀሙን ማወቅ ብቻ ነው፡፡

የየዋሕነቱ የልጅነት ጊዜ አልፎ የሚመጣው ታላቁ የወጣትነት ጊዜ በእግዚአብሔር ቃል ተቃኝቶ ዓላማ እንዲኖረው ከተደረገ ተአምር ይታይበታል፡፡ ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ የምንዘክራቸው ታላላቅ ሊቃውንት፣ ጻድቃን እና ሰማዕታት የቅድስናቸውን መሠረት በልጅነታቸው ጥለው አብቦ ያፈራው በወጣትነታቸው ነው፡፡

አቤል በእግዚአብሔር ዘንድ የተመሰገነውን መሥዋዕት ያቀረበው፣ ይስሐቅ ራሱን ለአምላኩ ለመሥዋዕትነት በፈቃዱ ሊሰጥ የተዘጋጀው፣ ያዕቆብ በፍኖተ ሎዛ እግዚአብሔርን ያገኘው፣  ዳዊት ለንጉሥነት የተጠራው፣ ሰሎሞን ለንጉሥነት በቅቶ ለጥበብ የታደለው፣ ዳንኤል በጥበብ እና በራእይ የበለጸገው፣ ሠለስቱ ደቂቅ ለሃይማኖታቸው በምድረ ባቢሎን ምስክር የሆኑት በወጣትነታቸው ጊዜ ነበር፡፡

ማርቆስ የግብጽን አምልኮ ጣዖት የሻረው፣ ዮሐንስ ወንጌል ያስተማረው፣ ጢሞቴዎስ ቅዱስ ጳውሎስን ተከትሎ የወጣው፣ ቲቶ የሐዋርያው የቅዱስ ጳውሎስን መልእከት በማድረስ ወንጌልን ያስፋፋው፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ በዱድያኖስ/ዲዮቅልጥያኖስ አደባባይ ለሃይማኖቱ ምስከር ሆኖ በሰማዕትነት ያለፈው፣ አርሴማ ንጽሕናዋን እና ሃይማኖቷን ለመጠበቅ ስትል በአርመኑ ንጉሥ በድርጣድስ አደባባይ መከራ የተቀበለችው፣ አትናቴዎስ በኒቂያ ጉባኤ አርዮስን ተከራክሮ የረታው በወጣትነታቸው ጊዜ ነበር፡፡

አቡነ ተክለ ሃይማኖት ለሐዋርያነት የተሠማሩት፣ አቡነ ዜና ማርቆስ ደቡብ ኢትዮጵያን ያስተማሩት፣ አቡነ አኖሬዎስ ባሌን በወንጌል ያበሩት፣ አቡነ ሳሙኤል ዋልድባን ያቀኑት፣ ላሊበላ ኢየሩሳሌም ድረስ በእግሩ የተጓዘው፣ አባ ጊዮርጊስ ሰዓታትን የደረሰው፣ ቅዱስ ያሬድ ዝማሬውን በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የቀመረው፣ በወጣትነታቸው ጊዜ ነበር፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን እና ሕዝቧን ያጠፉ፣ ሃይማኖታቸውን ክደው ለመከራ የተዳረጉ፣ ታሪክ በመጥፎ ሥራቸው የሚያስታውሳቸው እነ ይሁዳ እና ዴማስ፣ እነ አርዮስ እና መቅዶንዮስ፣ እነ ኔሮን እና ዲዮቅልጥያኖስ፣ እነ ሂትለር እና ሞሶሎኒ የክፋት ሥራቸውን ያደላደሉት በወጣትነታቸው ጊዜ ነበር፡፡

ለአምስት ዶሮዎች ሃያ ሽንብራ ቢበተንላቸው ስንት ስንት ይደርሳቸዋል ተብለው ሊቁ ቢጠየቁ እንደአለቃቀማቸው ነው አሉ ይባላል፡፡ ወጣቶችም የተሰጣቸውን ተፈጥሮአዊ ጸጋ ካወቁበት እና ለበጎ ዓላማ ለማዋል ከወሰኑ ዓለምን ከምሬት ወደ ጣፋጭነት፣ ከሞት ወደ ሕይወት፣ ከክፋት ወደ ደግነት ሊለውጥ የሚችል ተግባር ለመፈጸም ይችላሉ፡፡

የሀገራችን ገበሬዎች እርሻውን ሲያሳምሩት በሬውን ከወይፈን ጋር ይጠምዱታል፡፡ ይህም በመሆኑ በሬው ለወይፈኑ ቀንበር ያስለምደዋል፤ወይፈኑም ለበሬው ጉልበት ይሆነዋል፡፡ ወጣቶቻችንም ፍኖተ ሃይማኖትን ይዘው ከላይ ታሪካቸው እንደተጠቀሰው ወጣቶች ሁሉ በመጓዝ ቤተ ክርስቲያን የምትፈልግባቸውን ፍሬ እንዲያፈሩ የአበው ምክር እና አመራር ያስፈልጋቸዋል፡፡ ከላይም ያየናቸውና በወጣትነት ጊዜያቸው ሥራ ሠሩ ብለን ያመሰገንናቸው ወጣቶች የአባቶቻቸውን ምክር እና መመርያ በሚገባ ተቀብለው በተግባር ለማዋል በመብቃታቸው ነው፡፡ ስለዚህም የዛሬው ወጣት የአባቶቸን ምክር እና ተግሣጽ እየተቀበለ ቢሠራ የትናንቱን ታሪክ መድገም ፣ዛሬም አዲስ ታሪክ መሥራት ይችላል፡፡

ወጣቶች በኢ ትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ምን ሠርተዋል የወላጆችስ አስተዋጽዖ ምን ነበር

እስመ ጽሙአን ለትምህርት ብሔረ ኢትዮጵያ ኄራን፣ ደጎቹ የኢትዮጵያ ሰዎች ትምህርትን የተጠሙ ናቸው በማለት የ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ደራሲ ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ መጽሐፈ ብርሃን በተባለ ድርሰቱ እንደገለጠው፡፡ ኢትዮጵያውያን ወላጆች የትምህርትን ጥቅም አስቀድመው በማወቃቸው ልጆቻቸውን ቢበዛ ሰባት ዓመት ሲሞላቸው ወደ ትምህርት ቤት ይልኳቸው እንደነበር ገድላቱ ምስክሮቻችን ናቸው፡፡ ከታወቁት ሊቃውንት ቅዱስ ያሬድ እና አባ ጊዮርጊስ ወደ ትምህርት ቤት የገቡት በሰባት ዓመታቸው ነበር፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ዲቁና ተቀብለው ወደ አገልግሎት የገቡት በሰባት ዓመታቸው ነበር፡፡ የአሰቦት ገዳም መሥራቹ አባ ሳሙኤል ዘደብረ ወገግም ለትምህርት ደብረ ሊባኖስ የገቡት በሰባት ዓመታቸው ነበር፡፡ ከቅርብ ዘመን ሊቃውንት እነ መምህር ኤስድሮስ ወደ ትምህርት ቤት የገቡት በ11 ዓመታቸው ሲሆን፣ አቡነ አብርሃም ቀዳማዊ 1861 እስከ 1931 ዓ.ም ደግሞ በ17 ዓመታቸው ዜማ እና ቅኔን አጠናቅቀው ወደ ትርጓሜ መጻሕፍት ቤት ገብተው ነበር፡፡

በጥንቷ ኢትዮጵያ ወጣቶቹ ይማሩት የነበረው ትምህርት ሦስት ዓይነት ነበር፡፡ ለመተዳደርያ የሚሆናቸውን የግብርና ትምህርት፣ ሀገር ለመጠበቂያ የሚሆናቸውን የውጊያ ትምህርት እና ሃይማኖት ለመጠበቂያ የሚሆናቸውን የሃይማኖት ትምህርት፡፡ለምሳሌ ጻድቁ አባታችን ተክለ ሃይማኖት ገና በወላጆቻቸው ቤት እያሉ ፈረስ መጋለብን እና ቀስት መወርወርን የመሳሰለውን ሞያ ተምረው እንደነበር ገድላቸው ይነግረናል፡፡

በዚህ መንገድ የሰለጠኑት የሀገራችን ወጣቶች ውትድርናው ከሳባቸው ወደ ወታደርነቱ፣ግብርናውን ከወደዱ ወደ ግብርናቸው በሃይማኖት ፍቅር ከተነጠቁ ደግሞ ወደ አብነት ት/ቤቱ ከዚያም ወደምነናው ያመሩ ነበር፡፡ 

ሞፈር ጠምደው አርሰው፣ መሣርያ ታጥቀው አገር ጠብቀው፣ ኢትዮጵያን ኢትዮጵያ ያሰኟት እነዚህ ወጣቶች ነበሩ፡፡ በሀገራችን ታሪክ የምናደንቃቸው ነገሥታት ለዙፋን የበቁበትን ዕድሜ ብንመለከተው በወጣትነታቸው ዕድሜ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ የቴዎድሮስ ቀኝ እጅ የነበረው ገብርየ፣ ከጣልያን ጠፍተው ለዐፄ ምኒልክ ምሥጢር ያቀበሉትና ለዐድዋ ድል መገኘት አስተዋጽዖ ያደረጉት ሁለቱ የሐማሴን ተወላጆች፣ ሞሶሎኒን በአደባባይ የገጠሙት አብርሃም ደቦጭ እና ሞገስ አስገዶም፣ እነዚህ ሁሉ ወጣቶች ነበሩ፡፡ ርእሰ ጉዳያችንን እንዳንስት እንመለስ እንጂ ዛሬ ብዙዎችን እናነሣቸው ዘንድ ግድ ባለን ነበር፡፡

መቼም በሀገራችን በሬ ጠምዶ፣ ሞፈር ተሸክሞ፣ አውድማ ለቀልቆ፣ ጎተራ ሞልቶ፣ እህል አቅንቶ ሲያጠግበን የኖረው ገበሬ ታሪክ አልተመዘገበም፡፡ አንበሳ እና ነብር የገደሉትን ያመሰገንናቸውን ያህል ሕዝብ እንዳይሞት ያደረጉትን ገበሬዎች አላመሰገንናቸውም፡፡ ታሪካችንም በአብዛኛው የወታደሮች ታሪክ በመሆኑ ስለ ጀግና ገበሬዎች አልተጻፈም ለማለት ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ አባቶቻቸውን ተከትለው ገና በአምስት እና በስድስት ዓመታቸው ወደ ግብርና የሚገቡ ወጣቶች ባሉባት ኢትዮጵያ በወጣትነት ጊዜ የሚሠራውን ገድል መገመቱ ቀላል ነው፡፡

በአብነት ትምህርቱ ገፍተው በክህነት አገልግሎትም ሆነ በትርጓሜያት ሊቅነት የተመሰከረላቸው የቤተ ክርስቲያናችን አበው የወጣትነት ጊዜያቸውን ዕውቀት በመሸመት፣መምህሮቻቸውን እና ቤተ ክርስቲያናቸውን በማገልገል ነበር ያሳለፉት፡፡ ይህንን ሁሉ መልካም ፍሬ ለማፍራት የቻሉትም ከእግዚአብሔር ቸርነት ጋር የአባቶቻቸው ምክር፣ ክትትል እና እገዛ ስላልተለያቸው እነርሱም ተቀባዮች ስለነበሩ ነበር፡፡

እስከ አሥራ ዘጠነኛው መቶ ክፍለ ዘመን በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ወጣቶችን የምናገኛቸው በአብነቱ መሥመር ነበር፡፡ በአሥራ ዘጠነኛው መክዘ አዲሱ የትምህርት ሥርዓት በሃገሪቱ ሲዘረጋ ሁለት ዓይነት ትውልድን ፈጠረ፡፡ በአንድ በኩል በአብነቱ መሥመር ተጉዞ የቤተ ክርስቲያንን ዕውቀት እና ሞያ የተካነ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ዘመናዊ በሚባለው የትምህርት ሥርዓት ውስጥ ተምሮ ዘመናዊ የሚባለውን ዕውቀት እና ሞያ ሸምቶ በዘመናዊው ቢሮክራሲ ውስጥ የሚያገለግል ፡፡

 የትምህርት ሥርዓታችን ነባሩን መሠረት አድርጎ የጎደለውን ሞልቶ፣ ያለውን አካትቶ መጓዝ ሲገባው መቼም የነበረውን ጥለን ሌላ መሥርተን መጓዝ ልማዳችን ሆኗልና በሀገሪቱ ከዚህ በፊት ትምህርት ተሰጥቶ የማያውቅ ይመስል አዲስ የትምህርት ሥርዓት እና ይዘት ፈጥሮ እንዲያውም ከውጭ እንዳለ አስገብቶ ጀመረ፡፡ በዚህም የተነሣ  ከላይ ያየናቸውን የማይገጣጠሙ ሁለት ትውልዶች ፈጠረ፡፡

አብነታዊው ትውልድ ዘመናዊ ነኝ የሚለውን ኮቶሊክ፣ ጾም ሻሪ፣ ባህል ደፋሪ እያለ ሲወቅሰው፤ ዘመናዊ ነኝ ባዩ ደግሞ አብነታዊውን ድግምታም፣ ኋላቀር፣ ጎታች እያለ ይወቅሰው ነበር፡፡ አንድ ሆነው ለአንድ ሀገር መሥራት ይችሉ የነበሩት ትውልዶች በመተቻቸት እና እንደ ርብቃ ልጆች በመገፋፋት መንታ መሥመራቸውን ይበልጥ አጠነከሩት፡፡

በዚህ የተነሣ አብነታዊው ትውልድ ከዘመናዊው ትምህርት ርቆ፣ ዘመናዊውም ትውልድ ከአብነታዊው ትምህርት ርቆ ኖረ፡፡ ይህ ደግሞ በኋላ ለተፈጠረው እግዚአብሔር የለም ባይ ትውልድ መነሻ ሆነ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ቤተ ክርስቲያንን በተሳላሚነት እንጂ በተሳታፊነት እንዳናውቃት አደረገን፡፡ ቤተ ክርስቲያናችንም ሃይማኖት እንዳባቶቿ፣ ጥበብን ግን እንደዘመኗ ይዛ እንዳትጓዝ ዕንቅፋት ሆነባት፡፡ በአስተዳደር፣ በአሠራር፣ በአመራር፣ እና በአወቃቀር፤ በማኅበራዊ እና ኤኮኖሚያዊ አገልግሎት አኃት አብያተ ክርስቲያናት እና ሌሎችም ከደረሱበት ደረጃ ላይ እንዳንደርስ ያደረገንም ይሄ ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ እነዚህ ነገሮች ዘመናዊውን ትምህርት እና አሠራር በመጠየቃቸውና የዚህ ባለቤት የነበረው ትውልድም ከቤተ ክህነቱ ርቆ በመኖሩ ነው፡፡

በ1940ዎቹ ሰንበት ት/ቤቶች በማኅበራት ስም ሲደራጁ የነበራቸው ዋና ዓላማ ሁለቱን ትውልድ አቀራርቦ ወደ አንድ ወጥ ትውልድነት መቀየር ነበር፡፡ ሃይማኖቱን የሚያውቅ፣ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ያለው፣ በሌላ በኩል ደግሞ በዘመኑ ዕውቀት የበሰለ ሀገራዊ ሰው መፍጠር፡፡

ይህን መሰሉን ሰው ለማምጣት ሰንበት ት/ቤቶቻችን ባለፉት ሃምሳ ዓመታት በአባቶቻቸው ሥር በመታዘዝ፣መመርያን በመቀበል፣በሙሉ ዕውቀት እና ጊዜያቸው ብዙ ታግለዋል፡፡ በዚህ ተጋድሏቸው ምክንያትም ከመካከለኛው መክዘ በኋላ ቀዘቅዞ የነበረውን የስብከተ ወንጌል መርሐግብር አንቀሳቅሰዋል፣የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ዘመናዊ በሆነ የትምህርት አሰጣጥ መንገድ ለወጣቱ እንዲደርስ አድርገዋል፣ልዩ ልዩ የትምህርት መጻሕፍትን አዘጋጅተዋል፣ ወጣቱ ትውልድ በዝማሬ አገልግሎት እንዲሳተፍ አድርገዋል፡፡ ኮርሶችን፣ ሴሚናሮችን፣ ሥልጠናዎችን፣ ጉዞዎችን በማዘጋጀት ምእመናን ትምህርተ ቤተ ክርስቲያንን ምቹ በሆነ መንገድ እንዲያኙ አድርገዋል፡፡ ይህ ሁሉ ፍሬ ወጣቶች ከአባቶቻቸው ጋር በመሆን በታዛዥነት እና በአገልጋይነት መሥመር ባይሰለፉ ኖሮ፣አባቶችም ወጣቱን በመኮትኮት እና በማሠማራት ባይተጉ ኖሮ ባልተገኘ ነበር፡፡

        እስካሁን የሠራነው የሚያስመሰግን ቢሆንም በቂያችን ግን አይደለም፡፡ ቤተ ክርስ ቲያናችን ከተደቀኑባት ግልጽ
         እና ቅርብ ሦስት አደጋዎች ለመታደግ እና ጥንታዊውን ክብር እና ዝናዋን ለመመለስ ካልቻልን ድካማችን ሁሉ
         ከንቱ ይሆናል፡፡ 
  የወቅቱ የቤተ ክርስቲያናችን ሦስት ፈተናዎች የምንላቸው

        ቤተ ክርስቲያን በውጭ ሀገር በአስተዳደር፣ በሰው ኃይል እና በመዋቅር በሚገባ አለመደራጀቷ፣

        ቤተ ክርስቲያንን ለመከፋፈል እና ለመቀሰጥ የተነሡ ክፍሎች መኖራቸው፣

        ትናንት ሙስሊም እና ክርስቲያኑ ተባብረው እና ተፋቅረው ይኖሩባት በነበረች ኢትዮጵያ በአክራሪ ሙስሊሞች
          የተነሣ የሕዝቡ ፍቅር እና ሰላም እየተናጋ መምጣቱ፣

እነዚህን ፈተናዎች ለመቋቋም እንዲቻል ከወጣቶች አምስት ነገሮች ያስፈልጋሉ፤ እነዚህም፡-

        ዐውቆ እና ነቅቶ መገኘት፣

        ተዘጋጅቶ እና ሆኖ መገኘት፡

        ለተሳትፎ መዘጋጀት፡

        ዘላቂ ውጤት ሊያመጣ የሚችል ስትራቴጂ ነድፎ መንቀሳቀስ፡

        ኃይልን ማሰባሰብ ናቸው፡፡
ዐውቆ እና ነቅቶ መገኘት፡- ስንል ወጣቱ ትውልድ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት፣ ታሪክ፣ ቅርስ፣ ትውፊት፣ ባሕል እና ሀብት ዐውቆ መገኘት ማለት ነው፡፡ የማናውቀውን ነገር መረከብ፣ መጠበቅ፣ ማፍቀር፣ ለዚያም መሥዋዕትነት መክፈል አንችልም፡፡ ቢጠፋ መጥፋቱን፣ ቢበላሽ መበላሸቱን፣ ቢለወጥ መለወጡን መለየት የምንችለው አስቀድመን ካወቅነው ብቻ ነው፡፡ ዛሬ ቅርሳችንን በሚገባ ቆጥረን እና ሠፍረን ባለማወቃችን የጠፋውን እና የቀረውን ለማወቅ አልቻልንም፡፡ ትናንት የነበረ፣ ዛሬ ግን የቀረ፣ ትናንት ያልነበረ ዛሬ የተጨመረ፣ የኛ ያልሆነ ከሌሎች የመጣ፣ የኛ የሆነ ሌሎች የወረሱት ምንድን ነው) ብለን መለየት የምንችለው ስናውቅ ነው፡፡ ከቅዱሳት መጻሕፍት ዕውቀት በተጨማሪ የቤተ ክርስቲያንን ታሪክ እና ሀብት ለማወቅ የሚያስችሉ መንገዶችም መዘርጋት አለባቸው፡፡ ኤግዚቢሽኖች፣ ጉዞዎች፣ ጥናታዊ ጉባኤያት፣ ምርምሮች፣ ሊቃውንትን ጋብዞ መጠየቅ፣ ገዳማትን እና አድባራትን መጎብኘት እና ማጥናት፣ ሕገ ቤተ ክርስቲያንን፣ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን መጠበቅ፣ምክረ አበውን መጠቀም ለዚህ ይጠቅማሉ፡፡

ተዘጋጅቶ እና ሆኖ መገኘት፡- ክርስትና ሞያ፣ ፍልስፍና ወይንም ደግሞ ገጸ ባሕርይ አይደለም፡፡ በርግጥ ካልሆኑ በቀር መስለው ሊኖሩት አይቻልም፡፡ ውሳጣዊ ማንነትን ሌላ አድርጎ ውጫዊ ማንነትን በመቀየር አይኖርም፡፡ እንደሞያ የሚቀየር፣ እንደ ፍልስፍና የሚሻር፣ እንደ ገጸ ባሕርይ የሚያስመስሉት አይደለም፡፡ ክርስትና የተማሩትን ማመንን፣ ያመኑትን መሆንን ይጠይቃል፡፡ ክርስቲያን ሳይሆኑ ክርስቲያናዊ ሥራ መሥራትም አይቻልም፡፡

በመሆኑም ወጣቶች ራሳቸውን መንፈሳውያን ማድረግ አለባቸው፡፡ መንፈሳዊነት መንፈሳዊ ትምህርት መማር ብቻ ሳይሆን ቀደምት መንፈሳውያን እንዳደረጉት ከምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን መሳተፍ /በተለይ ቅዱስ ቁርባን እና ንስሐ/፣ መንፈሳዊ ሀብታትን /ጾም፣ጸሎት፣ ስግደት፣ ምጽዋት/ ገንዘብ ማድረግ፣ ከቤተ ክርስቲያን የጸሎት ሕይወት /ቅዳሴ፣ሰዓታት፣ማኅሌት፣ወዘተ/ መሳተፍ፣ የሥነ ምግባር እና የጠባይ ለውጥ ማምጣት ማለት ነው፡፡ 

ይህንን በመሰለው ሕይወት የጸና ወጣት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተገኘ መንፈሳዊ ወታደር ማለት ነው፡፡ ራሱን፣ ሕዝቡን እና ቤተ ክርስቲያኑን ከክፉው ፍላጻ ይጠብቃልና፡፡ ከመናፍቃን በትምህርት፣ከአጋንንት በጸሎት፡፡

ለተሳትፎ መዘጋጀት፡ ክርስቲያናዊ ሕይወት ሱታፌን ይጠይቃል፡፡ ሱታፌውም በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት መሳተፍ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን የነ እገሌ ብቻ ናት የምንላት አይደለችም፡፡ እንደየ ዐቅማችን እና ስጦታችን አስተዋጽዖአችንን የምናበረክትባት ቤት ናት፡፡ በክህነቱ አገልግሎት፣ ገዳማት አድባራትን በመርዳት፣ በማስተማር፣ በመጻፍ፣ በመዘመር፣ በጉልበት እና በዕውቀት አገልግሎት በመስጠት፣ ሞያችንን እና ችሎታችንን በመስጠት፣ በምንኩስናው እና በምናኔው ገብተን በማገልገል ነው የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት ለማጠናከር እና ልናይ የምንፈልገውን ማየት የምንችለው፡፡

ቁጭት እና ፍላጎት፣ ምኞት እና ሃሳብ ብቻቸውን ሥራ ሠርተው አያውቁም፡፡ የሚተገብራቸው ካላገኙ በቀር፡፡ ሺ ጊዜ ጨለማን ከመውቀስ አንድ ሻማ ማብራት ይሻላል እንዳለው ቻይናዊው ኮንፊሺየስ፣ እንዲህ ቢሆን ጥሩ ነው እያልን የምንናገረውን ራሳችን ለማድረግ ካልተነሣን ማን ነው የሚያደርግልን)

ይህ እና ያ ችግር አለ፣ ይህ እና ያ ችግር ካልተቀረፈ እንዲህ አላደርግም እያልን ብንተወው ችግሩ እየባሰ እንጂ እየተሻሻለ አይሄድም፡፡ ችግር በራሱ ጊዜ የሚሻሻል፣ መከራም በራሱ ጊዜ የሚያልፍ ቢሆን ኖሮ እነዚያ ሁሉ ሰማዕታት መሠዋት አያስፈልጋቸውም ነበር፡፡

ዘላቂ ውጤት ሊያመጣ የሚችል ስትራቴጂ ነድፎ መንቀሳቀስ፡

ወጣቱ ትውልድ ጊዜያዊ ከሆኑ እና በአንድ ወቅት ብቻ ደስታን እና ርካታን ከሚፈጥሩ ነገሮች ባሻገር ዘላቂ የሆነ ውጤት ያላቸው ነገሮች ላይ ማተኮር አለበት፡፡ ዛሬ የምናደርገው ነገር መሠረት ሆኖ የነገው ትወልድ ግድግዳውን፣ ቀጣዩም ትውልድ ጣራውን እንዲሠራው ሆኖ መዘጋጀት አለበት፡፡ አንዲት ገዳም በመርዳት፣ ችግር መጣ ሲባል የተወሰነ ብር በማዋጣት፣ የተወሰኑ መጻሕፍትን በማዘጋጀት፣ የአንድን አካባቢ የመዝሙር ሥርዓት ብቻ በማስተካከል፣ ራስን ከፈተና በመጠበቅ፣ ወዘተ ብቻ የቤተ ክርስቲያን ዕድገት አይመጣም፡፡

ነገስ ምን እንዲመጣ እንፈልጋለን) ይህንን ለማምጣት ምን ያስፈልገናል) በየትኛው መንገድ ብንጓዝ የተሻለ ውጤት እናስገኛለን) የኛ ደርሻ የት ድረስ ነው) የሚሉትን አጥንተን መጓዝ አለብን፡፡

በሰውነታችን ውስጥ ልዩ ልዩ ሥርዓቶች አሉ፡፡ የመተንፈስ፣ የደም ዝውውር፣ የነርቭ፣ የምግብ ውሕደት፣ ወዘተ፡፡ እነዚህ ሁሉ የሚሠሩት ግን የልብ እንቅስቃሴ ሲኖር ብቻ ነው፡፡ ዋናው የሰውነት ሞተሩ እርሱ ነው፡፡ እርሱ ከሞተ ተያይዞ መሞት ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያናችንም ዋናው ሞተሩ የሆነው የቤተ ክርስቲያን መዋቅር ተገቢ፣ ቀልጣፋ፣ ቀና እና ውጤታማ በሆነ መልኩ ካልተንቀሳቀሰ ሁላችንም በየበኩላችን የምናደርገው እንቅስቃሴ ውጤታማ አይሆንም፡፡

ከአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን እስከ ቅዱስ ሲኖዶስ ለሥራ አመቺ፣ ውጤታማ፣ ሃይማኖት ተኮር የሆነ፣ ደረጃውን የጠበቀ፣ ሁሉን ሊያሳትፍ የሚችል ጠንካራ የሥራ እና የአገልግሎት መዋቅር ካልተዘረጋ በስተቀር ትናንሽ ተግባራትን በመሥራት ለውጥ ማምጣት አይቻልም፡፡

ስለሆነም ጉዟችን ሁሉ አሐቲ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን እስከ መንበረ ፓትርያርክ በመዋቅር እና በአሠራረ ተጠናክራ ለማየት በሚያስችል ጎዳና ላይ መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ ለኛ ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ አካሉ የሆነች እና በደሙ የተዋጀች ቤታችን ናት፡፡ ከወገን፣ ከፖለቲካ እና ከዘር ጉዳይ ጋር ያልተቀላቀለች፣ ሃይማኖታዊ ቤት ናት፡፡

እናም ስሜታውያን ሳንሆን፣ በምንሰማቸው ሐሜቶች እና ወሬዎች ሳንደናገር ለአንዲት ቤተ ክርስቲያን መጠናከር እና አገልግሎት የሚያመች ዘላቂ ዕቅድ መንደፍ ያስፈልገናል፡፡ ይህ ዕቅዳችን ደግሞ ከአጥቢያዊነት ወጥተን፣ ከጠባብነት ርቀን የቤተ ክርስቲያንን መዋቅር ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ አጥቢያ ሊያጠናክር የሚችል መሆን አለበት፡፡

ኃይልን ማሰባሰብ       

ወጣቱ ትውልድ በልዩ ልዩ ዓይነት መንገዶች ተበትኖ ነው የሚገኘው፡፡ አንዳንዶቻችን በማወቅም ሆነ ባለማወቅ፣ ከተወገዙ መናፍቃን ጋር በመጓዝ ላይ  እንገኛለን፣ ሌሎቻችን ደግሞ እስከተወሰነ ጊዜ ድረስ ራሳችንን ከቤተ ክህነቱ አስተዳደር አግልለናል ብለናል፣ እስከ የሚለው ፍጻሜ ያለው እስከ ነው፣ ወይስ የሌለው የሚለው ባይታወቅም፡፡ ሌሎቹም በእናት ቤተ ክርስቲያን ሥር ነን የሚለው ቢያስመሰግነንም በአንዳንዶቻችን ዘንድ ግን በእናት ቤተ ክርስቲያን ሥር መሆናችንን በተግባር ሊያሳዩ የማይችሉ ነገሮች ይታያሉ፡፡ 

ይህ ሁሉ መበታተን ግን ሰይጣንን ብቻ ነው የሚጠቅመው፡፡ መናፍቃን እና አክራሪ እስላሞች ሳይግባቡ እየተግባቡ ኃይላቸውን አደራጅተው ቤተ ክርስቲያንን ለማፍረስ ሲረባረቡ እኛ በተለያየ መንገድ እየተጓዝን ድል ልንነሣቸው አይቻለንም፡፡ ለትልቁ ችግር ስንል ትንንሽ ችግሮቻችንን፣ ለትልቁ ጠላት ስንል ትንንሽ ጠቦቻችንን፣ ለትልቁ ሥዕል ስንል ትንንሽ ሥዕሎቻችን መተው ካልቻልን ራሳችንን በራሳችን ነው የምናጠፋው፡፡

እኛ ልዩነታችንን አስወግደን እስክንግባባ የሚጠብቅ ጠላት የለንም፡፡ መለያየታችንን ይጠቀምበታል እንጂ፡፡ ስለሆነም ነገ አይደለም ዛሬ፣ ወደፊት አይደለም አሁን ኃይላችንን ሰብሰብ አድርገን፣ ተባብረን እና ተዋሕደን የቤተ ክርስቲያንን አንድነት ለመጠበቅ በጽንዐት መቆም አለብን፡፡

እናም ነገ ዛሬ ሳንል ለቤተ ክርስቲያን አንድነት መቆም ይገባናል፡፡ በተለይም ወጣቱ ትውልድ የፖለቲከኞችን፣ የዘረኞችን ፣የአጽራረ ቤተ ክርስቲያንን ግፊት እና ተጽዕኖ ተቋቁሞ ለማታልፈው ቤተ ክርስቲያን የማያልፍ ሥራ ለመሥራት መነሣት አለበት፡፡

ነቢያት በቀየሱ ሐዋያት ገሠገሡ እንደተባለው ሁሉ፣ ለወጣቱ ውጤ ታማነት እና የዓላማ ጽናት የአባቶች መሪነት፣ አስተማሪነት፣ አርአያነት እና ግንባር ቀደምነት ወሳኝ ነው፡፡ አባቶች ከቀደምት አበው የተቀበልነውን ለተተኪው ትውልድ የማውረስ ኃላፊነት አለብን፡፡ ስለዚህም የቤተ ክርስቲያንን አንድነት እና አገልግሎት ለማጠናከር በሚደረገው ሁሉ አባቶች እና ልጆች የአባትነት እና የልጅነት ጠባያችን እንደ ቀድሞዎቹ አባቶች እና ልጆች ተገናዝቦ የቤተ ክርስቲያንን አንድነት ለማጠናከር በተጀመረው ሥራ የበኩላችንን እንድናደርግ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለ ወላዲቱ ድንግል ወለ መስቀሉ ክብር

  Listen Lesson of the week
  Listen Mesbak of the week
  Downlad Songs and Publications
  Discover Ethiopian Orthodox Church History
  Preaching of the week
 
  www.eotc-mkidusan.org
 
www.mahiberekidusan.org
  www.radiotewahedo.org
  www.tewahedomedia.org
Home| Feedback| Webmaster
EOTC-DC Diocese., All Rights Reserved